ከአዲስ አበባ የሸሸው የኮሮና ታማሚ ደብረ ብርሃን አካባቢ ተያዘ
ባለቤቱን ጨምሮ በተሳፈረበት ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ 13 ሰዎች እንዲሁም 6 ያደረበት ሆቴል ሰራተኞች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል
ግለሰቡ ትናንት አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ባደረገው ምርመራ በቫይረሱ መያዙን ያረጋገጠ ሲሆን ወደ ህክምና ተቋም ላለመግባት በሚል ነው የሸሸው
ወደ ህክምና ተቋም መግባት እያለበት ያመለጠው የቫይረሱ ታማሚ ደብረብርሃን አካባቢ ተያዘ
በኮሮና ቫይረስ መያዙን በምርመራ ቢያረጋግጥም ተለይቶ ሊታከም ወደሚችልበት የህክምና ተቋም ከመግባት ይልቅ ከአዲስ አበባ ያመለጠው ግለሰብ ደብረብርሃን አካባቢ ተይዟል፡፡
የቫይረሱን ምልክቶች ማየቱን ተከትሎ አዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የግል ሆስፒታል ትናንት ጠዋት አካባቢ የምርመራ ናሙናዎችን የሰጠው ግለሰቡ ከሰዓት መልስ አመሻሹ አካባቢ በቫይረሱ መያዙ በምርመራው መረጋገጡ ተነግሮት ለሚመለከተው አካል እንዲያሳውቅና ወደ ህክምና ተቋማት እንዲገባ ምክር ተለግሶት ነበረ፡፡
ሆኖም ምክሩን ያልተቀበለው ግለሰቡ ቀደም ሲል የተደወለበትን የእጅ ስልኩን በማጥፋት አመሻሽ አካባቢ አብራው ከነበረች ባለቤቱ ጋር በመሆን ይኖርበታል ወደ ተባለው ሸዋሮቢት ከተማ ያቀናል፡፡
ግለሰቡ እየመጣ እንደሆነ መረጃ የደረሰው የደብረብርሃን ከተማ ጤና ጽህፈት ቤትም ከሚመለከታቸው የዞንና የከተማው የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እና የጤና ባለሙያዎቹን በማዘጋጀት በቁጥጥር ስር ለማዋል ይሰናዳል፡፡ የከተማዋን መውጫና መግቢያ በሮች ጨምሮ በየአቅጣጫው ግለሰቡን ሲፈልግም ያመሻል ጽህፈት ቤቱን ዋቢ እንዳደረገው የከተማው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዘገባ ከሆነ፡፡
በጥብቅ ክትትል ውስጥ እንደሆነ ያወቀው ግለሰቡም እንዳሰበው ወደ ሸዋሮቢት ለመሄድ እንደሚቸገር ሲረዳ ደብረብርሃን ማደርን ይመርጣል፡፡ በርኖስ ከተባለ የከተማዋ ሆቴልም ያድራል፡፡
በጥብቅ እየተደረገ ካለው ክትትል ለማምለጥ በማሰብም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ አይሱዚ (ቅጥቅጥ) በተሰኘው የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ይሳፈራል፡፡
ሁኔታዎች እንደማይመቹ ሲረዳም መጀመሪያ ከተሳፈረበት ተሽከርካሪ ወርዶ በሌላ ተመሳሳይ ተሽከርካሪ በመሳፈር ወደ አዲስ አበባ መጓዙን ይጀምራል፡፡
ሆኖም ጥረቱ ከደብረ ብርሃን ከተማ በአዲስ አበባ መስመር ከ20 ኪሎ ሜትሮች በላይ እምብዛም ከማትርቀው ጫጫ ከተማ አልተሻገረም፡፡
በከተማዋ ሲደርስ ከነ ባለቤቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ደብረብርሃን ከተማ 07 ቀበሌ ጠባሴ ጤና ጣቢያ ወደሚገኘው የቫይረሱ ታማሚዎች ማታከሚያ ማዕከል እንዲገባ ተደረገ፡፡
አሽከርካሪውን ጨምሮ በቅጥቅጡ ተሳፍረው የነበሩ 13 ሰዎች እንዲሁም 6 የበርኖስ ሆቴል ሰራተኞችም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ወደሚገኘው ለይቶ ማቆያ ገብተዋል፡፡
ከ6ቱ የሆቴሉ ሰራተኞች ሁለቱ እንግዳ ተቀባይ፣ሁለቱ የጽዳት ሰራተኞች፣አንድ እንግዳ አስተናጋጅ እና አንድ የላውንደሪ ሰራተኛ መሆናቸውን የሆቴሉ ባለቤትና ስራ አስኪያ አቶ ደመረ ኃይሉ በግል የፌስቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል ።
በደብረ ብርሃን ከአሁን ቀደም በቫይረሱ የተያዘ አንድ ግለሰብ መገኘቱንና ቤተሰቦቹን ጨምሮ ንክኪ እንዳላቸው የተጠረጠሩ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡