“በግድቡ ላይ ውሳኔ የተላለፈው ፕሮጀክቱን ካስጀመሩ ሰዎች ጋር በመመካከር ነው”- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
“ውሃና መብራት ማግኘት ከማንም የማይለመን መሰረታዊ መብት” እንደሆነም አስቀምጠዋል
ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዓመት ያጋጠመውን አይነት የዲፕሎማሲ ፈተና አጋጥሞ አያውቅም
“በግድቡ ግንባታ ላይ ውሳኔ የተላለፈው ፕሮጀክቱን ካስጠኑና ካስጀመሩ ሰዎች ጋር ውይይት ተደርጎ ነው”- ዐቢይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ማብራሪያን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) “የለውጡ አመራር የሕዳሴ ግድብን አሳልፎ ሰጥቷል፣ በሉዓላዊነት ላይ ተደራድሯል” በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ፕሮጀክቱ በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በ2007 ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ኃይል እንዲያመነጭ ብሎም በ2009 ደግሞ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ወጥቶ እንደነበር ያነሱ ሲሆን “ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ቢሆን ኖሮ ይህንን ያህል ነገር አንባልም ነበር” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ግድቡ ስድስት ዓመታትን መዘግየቱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ምክንያት ሀገሪቱ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር በድምሩ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ማጣቷንም አስታውቀዋል፡፡ ግንባታው በመጓተቱ ምክንያትም “ብዙ ገንዘብ ወጪ እየተደረገ ነው”ም ብለዋል፡፡
በግንባታ ፕሮጄክቱ 8 ኮንትራት እና 6 ተቋራጮች እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሁን ላይ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለውን ግድብ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ያሉት ኢ/ር ክፍሌ ሆሮም ከዚህ በፊት ጊቤ አንድና ጣና በለስን እንዲሁም ሕዳሴን ያስጀመሩ በመሆናቸው ሥራውን በብቃት እያከናወኑና አፈጻጸሙንም ለመንግስት ሪፖርት እያደረጉ ናቸው ብለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዓመት ያጋጠመውን አይነት የዲፕሎማሲ ፈተና አጋጥሞ እንደማያውቅ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ የሆነውም “በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ያሉት አሁን በመሆኑ ነው” ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱን ካጠኑ፣ ለመንግስት ካቀረቡና ካስጀመሩ ሰዎች ማለትም በወቅቱ የውኃና ኢነርጅ ሚኒስትር ከነበሩት አለማየሁ ተገኑ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምህረት ደበበ እና የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት ግርማ ብሩ ጋር ውይይት መደረጉንና መሃል ላይ ለምን ተበላሸ፣ ችግሩ ምንድነው በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ውይይት መደረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
ግንባታው ሲጀመር የነበሩ የውጭ ዜጎችም ጭምር በውይይቱ መሳተፋቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጀመሪያውና ያጋጠመው ችግር መጀመሪያ ኮንትራት ወስዶ የነበረው ተሰርዞ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ያኔ ነው ነገሩ የተበላሸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ አካባቢ የለውጡ አመራር ሲሰራ የነበረው “ችግሩ ምን እንደሆነ መለየት ነበር” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
በተደረገው ውይይትና ግምገማ ፕሮጀክቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ቶሎ ማለቅ እንዲችል ብቃት ያለው ኃይል ገብቶ እንዲሰራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የአመራርና የኮንትራት ለውጥ መደረጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የለውጥ አመራሩ ከመጣ ወዲህ በየሳምንቱ ሳይቆራረጥ ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል፡፡ ቦርዱም በሳምንት ሁለት ጊዜ ጉዳዩን እንደሚያይና የፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጁ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ በየዕለቱ ሪፖርት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
ሕዳሴ ከለውጡ በኋላ ያለው አፈጻጸም
ዶ/ር ዐቢይ ዋናው ግድብ የመጀመሪያው ኃይል የማመንጫ ሥራ የሚጀመርበት ቦታ በጣም ታች እንደነበረ የገለጹ ሲሆን ይህም ከመጀመሪያው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ስላልተሰራ ቦታውን ከ525 ሜትር ማሳደግ አልተቻለም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሲቪል ስራውን የሚሰራው የጣሊያ ሳሊኒ ኢምፕሬጂሎ ክፍት የሆነበትን ቦታ ሞልቶ ኤሌክትሮ መካኒካል የሚሰራበትንና በሜቴክ የተያዘውን ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ተጨማሪ 35 ሜትር በመስራት 560 ሜትር እየደረሰ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ የተሰራው 25 ሜትር ብቻ እንደነበር እና በአንድ ዓመት ተኩል ግን 35 ሜትር መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ሜቴክ እንዲሰራ ተሰጥቶ የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ከምንም መጀመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሰራውና የተበየደው ችግር እንደነበረበትና እንዳለ መነሳቱንና ስራው እንደ አዲስ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ክረምት በሰኔ መጨረሻ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ (የጊቤ ቁጥር 1 ሦስት እጥፍ) ለመያዝ መታቀዱን ፣በቀጣይ ተጨማሪ 35 ሜትር በመጨመር 595 ሜትር ሲደርስ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ውኃ (የጊቤ ቁጥር 3 በላይ ሦስት እጥፍ) ውኃ ይያዛል ብለዋል፡፡ ተጨማሪ 45 ሜትር በማድረስ አጠቃላይ 645 ሜትር በማድረስ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ሜትር ውኃ መያዝ እንዲችል እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
“ከለውጥ በኋላ ሕዳሴ ግድብ ከሞት አገግሟል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ከጥፋት እንዲድን መደረጉን እና የምክር ቤቱ አባላት ይህንኑ በስፍራው ተገኝተው እንዲመለከቱ ጋብዘዋል፡
ዲፕሎማሲ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ግድቡን በመስራታችን የምንጎዳው ሀገር የለም” ብለዋል፡፡
“እያልን ያለነው መብራትና ውሃ የማያገኙ ዜጎቻችን ይጠቀሙ ነው” ያሉም ሲሆን ይሁ “ከማንም የማይለመን መሰረታዊ መብት” እንደሆነ አስቀምጠዋል፡፡
“ማገዝ የፈለገ ጎረቤት ያግዘን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ይህንን ማድረግ ያልቻለ ግን ተፍጨርጭረን እንድንወጣው ይተወን” ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡
“በግድቡ ላይ የሚደራደረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ነው” የሚለው ሃሳብ የተሳሳተ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ እየዋለ ያለና የተደራዳሪዎቹንም ሞራል ሊጎዳ የሚችል ነገር እንደሆነ ተናገሩት ዶ/ር ዐቢይ በዚሁ ላይ የሚደራደረው ኃይል አልተቀየረም ያሉ ሲሆን “ሌት ከቀን የሚሰሩ” ያሏቸውን ተደራዳሪዎች አመስግነዋል፡፡
የለውጥ አመራሩ ግንባታውን አጠናቆ ግድቡን ለህዝበ እንደሚያስረክብም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቡት፡፡
ኢትዮ-ሱዳን
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሱዳንና ኢትዮጵያን ዘመናትን የተሻገረ ግንኙነት አንስተዋል፡፡
የሱዳን ህዝብ ወንድምና ባለውለታም ነው ያሉም ሲሆን ሱዳን የሚለው ቃል በአረብኛና ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በግሪክ አንድ ትርጉሙ እንዳለው አስቀምጠዋል፡፡
ሃገራቱ የሚጋሩትን ረዥም ድንበር በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄም ለጦርነት የሚጋብዝ ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
“ሱዳን የኢትዮጵያ ሁነኛ ወዳጅ” ናት ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ሃገራቱ ወደ ውጊያ እንዲገቡ የሚፈልጉ አካላት የሉም ማለት እንዳልሆነ አስታውሰዋል፡፡
“ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያዋጋው ድንበር ከሆነ ከኢትዮጵያ በባሰ ከግብጽ ጋር የሚያከራክር ቦታ አለ” በሚል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንበር የውጊያ ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እና ሰፊ ንግግር መደረጉን አንስተዋል፡፡
ዶ/ር አቢይ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ጥያቄ ያላቸው ሱዳኖች በገላጋይ ዳኛ እንዳኝ የሚል ጥያቄ እንዳላቸው ያነሱም ሲሆን መግባባት ላይ መድረስ ማይቻል ከሆነ ግን የአፍሪካ ሕብረት ገብቶ ጉዳዩን እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡