“የህዳሴው ግድብ በሱዳንና በግብጽ ካሉት ግድቦች የተሻለ ደህንነት አለው”-የሱዳን የውሃ ሚኒስትር
“ግድቡ እንደሚጠቅመን ስንናገር ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆምን ተደርገን እንከሰሳለን”
የግንባታ ሂደቱን ዘመናዊነት፣ግልጋሎት ላይ የሚውሉትን ግብዓቶች እና ቴክኖሎጂዎች በምክንያትነት አስቀምጠዋል
“የህዳሴው ግድብ በሱዳንና በግብጽ ካሉት ግድቦች የተሻለ ደህንነት አለው”-የሱዳን የውሃ ሚኒስትር
ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሱዳንና በግብጽ ካሉት ግድቦች የተሻለ ደህንነት እንዳለው የሱዳን የመስኖና ውሃ ሃብቶች ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር መሃመድ አባስ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት እንግዳ ሆነው ከሃገራቸው ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
አባስ በቆይታቸው “የህዳሴው ግድብ የደህንነት ደረጃ ከሱዳን ግድቦች እና ከግብጽ ታላላቅ ግድቦች የተሻለ እንደሆነ በጥናት መረጋገጡን” ገልጸዋል እንደ ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ፡፡
ለዚህም የግንባታ ሂደቱን ዘመናዊነት፣ ግልጋሎት ላይ የሚውሉትን ግብዓቶች እና ቴክኖሎጂዎች በምክንያትነት አስቀምጠዋል፡፡
“ለራሳችን ጥቅሞች ብቻ ነው የምንወግነው፤ ውግንናችን አንዳንድ ጊዜ ከግብጽ ወይ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ሊሄድ ይችላል፤ ግድቡ እንደሚጠቅመን ስንናገር ከኢትዮጵያ ጎን እንደቆምን ተደርገን እንከሰሳለን” ሲሉም ነው አባስ የሚያክሉት፡፡
ኢትዮጵያ ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰስ ሃገራት ላይ “ጉልህ ጉዳት”ን እንደማያደርስ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡
የሶስትዮሽ የቴክኒክ ውይይት እንዲቀጥል ስምምነት ላይ መድረሳቸውም አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ውይይቱ እንዴት እና መቼ ይቀጥላል ስለሚለው ጉዳይ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ከሰሞኑ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በምን አግባብ፣እንዴት እና መቼ የቀጥላል ሚለው የውይይቱ ዝርዝር ጉዳይ ወቅቱ ሲደርስ በተደራዳሪዎች እንደሚወሰን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡