“ጉዳዮቹ የግድቡን አጀንዳ ወደ ድንበር አጀንዳነት ለማምጣት በማሰብ የተደረጉ ናቸው”- አቶ ንጉሱ ጥላሁን
“ከሱዳን ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ሲናፈሱ የሰነበቱት ጉዳዮች የግድቡን አጀንዳ ወደ ድንበር አጀንዳነት ለማምጣት በማሰብ የተደረጉ ናቸው” አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣
ከተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን “ከሱዳን ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ሲናፈሱ የሰነበቱት ጉዳዮች የግድቡን አጀንዳ ወደ ድንበር አጀንዳነት ለማምጣት በማሰብ የተደረጉ” እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ሱዳንና ኢትዮጵያ አመታትን የዘለቀ ጠንካራ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት አላቸው ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊው ግጭት እንዲቀሰቀስ በማሰብ የተዛቡ መረጃዎችን በስፋት ለህዝቡ በሚያደርሱ የሶስተኛ ወገን ሚዲያዎች መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ሃገራቱ ባላቸው ጠንካራ ግንኙነት ምክንያት የሚጋሩት ረዥም ድንበር እንኳን ሳይካለል 126 ገደማ ዓመታትን ዘልቋል ያሉት አቶ ንጉሱ ከሰሞኑም “ሃገራቱን የሚያጋጭ ይህ ነው የሚባል የጥቅም ግጭት የለም” ብለዋል፡፡
ምናልባትም “ከልክ በላይ” በሚዲያው መራገባቸው “ኢትዮጵያ በሌላት ባህሪና መገለጫዋ ባልሆነው ወራሪ ተደርጋ እንድትወሰድ በሚሰሩ አካላት የተደረገ” መሆኑንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡
ሆኖም የሃገራቱን የዘለቄታ ግንኙነት እና የጋራ ጥቅም በሚያስተሳስር መልኩ ግጭቱ እንዲፈታ የሃገራቱ ህዝብና መንግስታት ፍላጎት በመሆኑ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሱዳን የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት እንዳይጀመር ጠይቃለች በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ኢትዮጵያ ህዝቧን እንጂ ማንንም ተማምና ግድብ መገንባት አልጀመረችም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
“ግድቡን እንደማንኛውም ሃውልት አቁመን ልንመለከተው ወይም ሙዚዬም ልናደርገው አልገነባነውም” ያሉም ሲሆን “በራሳችን አቅም እንፈጽመዋለን ይህን ምናደርገው ግን ሌሎችን ለመጉዳት አይደለም” ብለዋል፡፡
“ሱዳን አይሞላም፤በስራ ላይ አይውልም አለች ማለት የኢትዮጵያን ጥቅም ተጋፋች ሳይሆን የራሷን የሱዳናውያንን ጥቅም ተጋፋች ማለት ነው” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
የቴክኒክ ውይይቱን በተመለከተ እንዲቀጥል በሁለቱ ሃገራት ማለትም በሱዳንና በግብጽ በኩል ፍላጎት አለ ያሉት አቶ ንጉሱ የስምምነቱን ዝርዝር ጉዳይ በምን አግባብ፣እንዴት እና መቼ እንደሚቀጥል ወቅቱ ሲደርስ በተደራዳሪዎች እንደሚወሰን ተናግረዋል፡፡