በሚሰራበት የሰዎች መታከሚያ ሆስፒታል ድመቱን ያከመው ሀኪም
የሆስፒታሉ ሀላፊዎች ጉዳዩን እንደሚመረምሩ አሳውቀዋል

ለሰው ልጆች ህክምና በሚል በተገነባው ሆስፒታል ድመት ያከመው እና መነጋገሪያ የሆነው ይህ ሐኪም ድመቷን ያከምኩት "ልትሞት በጣር ላይ ስለነበረች ነው" ብሏል
በሚሰራበት የሰዎች መታከሚያ ሆስፒታል ድመቱን ያከመው ሀኪም
ዶክተር ጊያንሉቻ ፋኔሊ የተባለው ጣልያናዊ ሐኪም ሲሆን በሰሜናዊ የሀገሪቱ አካባቢ በህክምና ሙያ ይተዳደራል።
ይህ ሰው ከሰሞኑ ያደረገው አነጋጋሪ ድርጊት ጣልያንን ጨምሮ በመላው አውሮፓ መነጋገሪያ ሆኗል።
የሚያሳድጋት ድመት ከጣሪያ ላይ ወድቃ ጉዳት ደርሶባታል ያለው ሐኪሙ ወደ ሚሰራበት ሆስፒታል በመውሰድ አክሟታል ተብሏል።
ግለሰቡ ድመቷ በደረሰባት ጉዳት ለመተንፈስ ተቸግራለች በሚል ሰዎችን በሚያክመው ሲቲ ስካን ህክምና እንዳደረገላትም ተገልጿል።
ሐኪሙ ድርጊቱን ለምን እንዳደረገው በጻፈው ማመልከቻ ላይ እንደገለጸው "ድመቷ ለእኔ እና ልጆቼ እጅግ አስፈላጊ በመሆኗ በማንኛውም መንገድ ህይወቷን ማትረፍ ስለ ነበረብኝ አድርጌዋለሁ" ብሏል።
የሁለት ዓመት እድሜ አላት የተባለችው ድመቷ በተደረገላት የሲቲ ስካን ህክምና ሳምባዋ ውሀ በመቋጠሩ መተንፈስ ከልክሏት እንደነበር ተገልጿል።
የኦስታ ሆስፒታል ሀላፊዎች በበኩላቸው ሐኪሙ በሰው ህክምና መስጫ ሆስፒታል ላይ ባደረገው የእንስሳት ህክምና አገልግሎት የተጣሰ አሰራር ካለ እንመረምራለን ብለዋል።
ጣልያናዊያን በበኩላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሐኪሙን ተቃውመው እና ደግፈው አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው።
ለሰው በተዘጋጀ ሆስፒታል ላይ እንስሳትን ማከም ትክክል አይደለም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ሲኖሩ ቀሪዎቹ ደግሞ ሐኪሙ በማንኛውም መንገድ ህይወት ማትረፉ ጀግና ያስብለዋል እያሉ ነው።
የሐኪሙ ሚስት ነች የተባለችው ሴት በበኩሏ ባሏ የሰራው ስራ ጀግና የሚያስብለው እና የሚያሸልመው እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም ማለቷን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል