የጣልያን ፖሊስ አንድ መነኩሴን ከወንበዴዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል አሰረ
መነኩሲቷ በጣልያን በእስር ላይ ለሚገኙ ታራሚዎች ባደረጉት ድጋፍ ዓለም አቀፍ ሽልማትን በቅርቡ አሸንፈው ነበር

ፖሊስ መነኩሲቷ በእስር ላይ ያሉ ወንበዴዎችን በውጭ ካሉ አጋሮቻቸው ጋር እንዲገናኙ ሲሰሩ ነበር ብሏል
የጣልያን ፖሊስ አንድ መነኩሴን ከወንበዴዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል አሰረ።
የ57 ዓመት እድሜ ያላቸው አና ዶኔሊ ጣልያናዊት ሲሆኑ በሀገሪቱ ስመ ጥር የሀይማኖት ሰው ናቸው።
መነኩሲቷ ዶኔሊ በተለይም በሰሜናዊ ጣሊያን በእስር ላይ ያሉ ታራሚዎችን በመርዳትም ይታወቃሉ።
ታራሚዎች የተሻለ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ እና መንፈሳዊ እንዲሆኑ ላደረጉት ድጋፍም በቅርቡ ዓለም አቀፍ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የጣልያን ፖሊስ ግን እኝህ መነኩሲት ከአደገኛ ወንበዴዎች ጋር ግንኙነት አላቸው ሲል በወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ መነኩሲቷ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ታራሚዎች በውጭ ካሉ የወንጀል ተባባሪዎቻቸው ጋር መልዕክት ያደርሳሉ ተብለዋል።
በውጭ ያሉ ወይም ያልተያዙ ማፊያዎች በመነኩሲቷ አማካኝነት በእስር ላይ ያሉ ወንጀለኞች ጋር እየተነጋገሩ ወንጀል እየሰሩ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።
መነኩሲት ዶኔሊ የሀይማኖት ሰው መሆናቸውን ተከትሎ ለታራሚዎች መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ በብዙ እስር ቤቶች እንዲገቡ እና እንዲወጡ ፈቃድ አላቸው።
ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ክትትል መነኩሲቷን ጨምሮ 25 ሰዎች እና ከ2 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገንዘብ በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል።
ፖሊስ የወንበዴዎችን ትስስር ለመቆራረጥ በሚል ባደሩገው ክትትል መነኩሲቷ ከማፊያዎቹ ጋር አብራ እንደምትሰራ የሚያሳይ መረጃ እንዳገኘም አስታውቋል።