አሜሪካ የሶስቱን ሀገራት ወታደራዊ ስምምነት እንደምትደግፈው አስታውቃለች
ብሪታንያ፣ ጃፓን እና ጣልያን የጋራ ተዋጊ ጄት ለማምረት ተስማሙ።
ሶስቱ የአውሮፓ እና እስያ ሀገራት በጋራ የሚመራ አየር ሀይል ለማዋቀር መስማማታቸውን አስታውቀዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ይህ የጋራ የጦር አውሮፕላን ማምረት ስምምነት በብሪታንያ የሚመራ ሲሆን ጃፓን እና ጣልያንም የየራሳቸው ሚና አላቸው።
ግሎባል ኮምባት ኤር ፕሮግራም የተሰኘ ስያሜ ባለው በዚህ ስምምነት መሰረት ሶስቱ ሀገራት በፈረንጆቹ 2035 ላይ የጋራ የጦር አውሮፕላን ምርት ይጀምራሉ።
የጦር አውሮፕላኖቹን የብሪታንያው ቤ ሲስተም፣ የጃፓኑ ሚትሱቢሺ እና የጣልያኑ ሊኦናርዶ የተሰኙት ኩባንያዎች ያመርታሉ ተብሏል።
የዚህ ስምምነት አካል የሆነችው ጃፓን መሰል ወታደራዊ ህብረትን ስትቀላቀል ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የመጀመሪያዋ እንደሆነ ተገልጿል።
የጃፓንን ስምምነት መቀላቀል ተከትሎ ከዓመታዊ በጀቷ ላይ ሁለት በመቶው ያህሉን ለመከላከያ መመደብ የሚያስችላትን የህግ ማሻሻያ እንደምታደርግ ይጠበቃል።
አሜሪካ የሶስቱን ሀገራት ወታደራዊ ስምምነት እንደምትደግፈው የገለጸች ሲሆን ሌሎች ሀገራትም ይህን ስምምነት እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል ተብሏል።
ጃፓን የዚህ ወታደራዊ ስምምነት አካል መሆኗ ከጎረቤቷ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ሊደርስባት የሚችለውን ወታደራዊ ስጋት ሊያረግብላት እንደሚችል ተገልጿል።