የወቅቱን አነጋጋሪ የኤአይ መተግበሪያ "ዲፕሲክ" እንዴት መጠቀም ይቻላል?
በ6 ሚሊየን ዶላር ወጪ የተሰራውና ከሰሞኑ ከወደ ቻይና የተዋወቀው "ዲፕሲክ" ታዋቂዎቹን የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አስደንግጧል
መተግበሪያው በቀላሉና በነጻ የምንፈልገውን መረጃ ማቅረቡም ተመራጭ እንዳደረገው እየተነገረ ነው
የቻይናው "ዲፕሲክ" የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) መተግበሪያ የቻትጂፒቲ እና ጂሚኒ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ብሏል።
ከአሜሪካዎቹ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መተግበሪያዎች እጅግ ባነሰ ቴክኖሎጂና ወጪ የተሰራው መተግበሪያ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት አግኝቷል።
"ዲፕሲክ" በቀናት ውስጥ ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች ከአፕ ስቶር ላይ ያወረዱት ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ቀዳሚው ተፈላጊ መተግበሪያ ሆኗል።
እንደ ኦፕንኤአይ፣ አልፋቤት እና ሜታ ያሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች በቢሊየን ዶላር አውጥተው ያስተዋወቋቸውን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየተፎከከረ የሚገኘው "ዲፕሲክ" የወጣበት 6 ሚሊየን ዶላር ብቻ መሆኑ ተነግሯል።
መተግበሪያው ለአጠቃቀም ቀላል ሆኖ እነቻትጂፒቲ እስከ 200 ዶላር ክፍያ ጠይቀው የሚያቀርቡትን አገልግሎት በነጻና በተሻለ ጥራት ማቅረቡም ተመራጭ እንዳደረገው ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
የበርካታ ቋንቋዎች ሞዴሎች በመያዝ የሚሰራው "ዲፕሲክ" እንደ አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና ትግርኛ ላሉ ቋንቋዎችም ይበልጥ "አመቺ" መሆኑም ነው የተዘገበው።
በፈረንጆቹ 2023 በደቡባዊ ቻይና ሀንግዡ ግዛት ሊንግ ዌንፌግ በተባለ ባለሙያ የተሰራው "ዲፕሲክ"፥ የበርካታ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የተያያዘ ስራን የሚከውኑ ኩባንያዎችን የአክሲዮን ገበያ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል።
"ዲፕሲክ" ቻይና ከአሜሪካ ቺፖችን እንዳታስገባ የተጣለባትን ገደብ አምልጦ በርካሽ ቺፖች መሰራቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያፈሰሱ ኩባንያዎችን አሳስቧል።
"ዲፕሲክ አር1" እንዴት ይሰራል?
የቻትጂፒቲ ገጽታ ያለው "ዲፕሲክ" በኮምፒውተሮች እና ሞባይል ስልኮች ላይ በቀላሉ ይሰራል ተብሏል።
በኮምፒውተር ለመጠቀም በመጀመሪያ ወደ ዲፕሲክ ይፋዊ ድረገጽ መግባት ነው። ከዚያም የኢሜል አድራሻ አልያም ስልክ ቁጥር አስገብቶ አገልግሎቱን ማስጀመር
በኮምፒውተር ላይ መተግበሪያውን ከከፈትን በኋላ የምናገኘው ገጽ ለቻትጂፒቲ ተጠቃሚ እንግዳ አይሆንም።
በሞባይል ስልክ ላይም መተግበሪያውን ከአፕ ወይም ፕሌይስቶር ላይ በማውረድ መጠቀም ይቻላል። አጠቃቀሙም ከላይ እንደተጠቀሰው ነው፤ የኢሜል አድራሻን ወይም የስልክ ቁጥርን ማስገባትና አካውንት መክፈት በቂ ነው።
መተግበሪያው ጥያቄ ሲቀርብለት እንደ ሰው ልጅ አስቦ እንደሚመልስ ለማመላከትም "እያሰብኩ ነው" ("ቲንኪንግ") ብሎ ምላሹን በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ይዘረግፈዋል።
"ዲፕሲክ" እስካሁን ከደህንነት ጋር የተያያዘ ስጋት ባይቀርብበትም የቻይና እንደመሆኑ በአሜሪካ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግበት ይታመናል።