ኦነግ የዝቋላ ገዳም የኃይማኖት አባቶች ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲመረመር ጠየቀ
ኦነግ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም አይነት ግድያ እንደሚያወግዝ አስታውቋል
የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰላምና ጸጥታ ቢሮ የኃይማኖት አባቶች ግድያን የፈጸመው “ኦነግ ሸኔ” ነው ብሏል
የኦሮሞ ነጻት ግንባር (ኦነግ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የዝቋላ ገዳም የኃይማኖት አባቶች ግደያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠየቀ።
የሀይማኖት አባቶቹ የተገደሉት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባሳለፍነው ሃሙስ ባወጣቸው መግለጫ፤ “በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ አራት አባቶችን መግደሉን ገዳሙ አስታውቋል” ብላለች።
ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ታጣቂዎቹ ሦስት አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ከወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያርግበት ወቅት የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ አባቶችን በመያዝ ግድያ መፈጸሙን ቤተ ከርስርቲያኗ አስታውቃለች።
የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃሙስ ምሽት ባወጣው መግለጫው “በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አገልጋይ የሆኑት አራት የገዳሙ አባቶች በአሽባሪዉ ኦነግ ሸኔ መገደላቸዉ ታውቋል” ብሏል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ የሚጠራው እና መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው እና “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራው ቡድን የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የኃይማኖት አባች ግድያን አስመልክቶ እየቀረበበት ላለው ክስ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
የኦሮሞ ነጻት ግንባር (ኦነግ) ዛሬ ባወጣው መግለጫው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ካህናት ግደያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥያቄ አቅርቧል።
ኦነግ በመግለጫው “በዚሀ ሳምንት ማገባደጃ ላይ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራት ካህናት እንደታፈኑባት እና ከዚያ በኋላ መገደላቸውን ባወጣችው መግለጫ ሰምተናል” ብሏል።
“የኦሮሚያ በሄራዊ ክለላዊ መንግስት “ሰላምና ፀጥታ ቢሮ" ዜናውን አረጋግጦ ድርጊቱን የፈጸመዉ 'ሸኔ' የሚባል የታጠቀ ቡድን ነው በማለት ወቅሷል” ብሏል መግለጫው።
ኦነግ በንጹሃንና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት ግድያ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥቃቶችን እንደሚያወግዝም በመግለጫው አስታውቋል።
“በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመው የዘፈቀደ ግድያ እና ሌሎችም ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እና በገለልተኝነት እንዲጣራ ጠይቋል” ኦነግ መግለጫው።
“በካህናቱ ላይ ለተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ኃላፊነት መውሰድ ያለበት የክልል እና የፌደራል መንግስት እና የየራሳቸው መዋቅር ነው” ብሏል።
መንግስት እንደዚህ አይነት የወንጀል ድርጊቶችን በመወቃቀስ እና በመሸፋፈን ማለፉን አቁሞ በምርመራ እንዲጣራ ጉዳዩን ለገለልተኛ አካል ክፍት እንዲያደርግም ኦነግ በመግለጫው ተይቋል።
“መንግስት በስህተትም ይሁን እያወቀ ‘ሸኔ’ እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትም በተመሳሳይ ለሚደረገው ገለልተኛ ምርመራ መተባበር አለበት” ሲልም ኦነግ ጥሪ አቅርቧል።
ኦነግ በመግለጫው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተፈጸመውን አሰቃቂ የአየርና የሰው አልባ አውሮፕላን ድብደባ እና የጅምላ ግድያ ድርጊት ከማውገዝ ተቆጥባለች ወይም መርጣ ተናግራለች” ሲል ወቅሷል።
በመሆኑም “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶችና ሁከቶች ውስጥ እንደ ሰላም ፈጣሪ አካል የምትጫወተውን ሚና እንደገና ልታጤን ይገባል” ሲልም አሳስቧል።