የኮሮና ቫይረስን የመራባት ሂደት የሚገታው አዲስ መድሃኒት - “ዲ ኤፍ ኮቭ 01”
መድሃኒቱ የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያሳድግ ሳይሆን የቫይረሱን መስፋፋት የሚያቋርጥ ነው ተብሏል
አል አይን ኒውስ መድሃኒቱን ካስተዋወቁት ተመራማሪዎች መካከል ከዶክተር ጎርደን ፍሪማን ጋር ቆይታ አድርጓል
ከ6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን የገደለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም የአለማችን አሳሳቢው ጉዳይ ሆኗል።
ዳግም የስርጭት አድማሱን ማስፋቱም አለም ከሁለት አመት በፊት ወደነበረችበት ልትመልስ ይሆን? የሚል ጥርጣሬን እያስከተለ ነው።
ለቫይረሱ መከላከያ የተሰጡ ክትባቶችና ከዚያም በኋላ የተሰራጩ መድሃኒቶች ውጤታማነትም ማጠያየቁን ቀጥሏል።
የሰውነትን የብሽታ መከላከል አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮሩ (አንቲቦዲ) መድሃኒቶች ኮቪድ 19ኝን የመከላከል አቅማቸው በተዳከመበት ጊዜ በአሜሪካ ተመራማሪዎች አዲስ መድሃኒት ይፋ ተደርጓል።
የዳና ፋርበር የካንሰር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ያስተዋወቁት መድሃኒት “ዲ ኤፍ ኮቭ 01” ይሰኛል።
ስለ አዲሱ የኮሮና መድሃኒት ከተመራማሪዎቹ ውስጥ አንዱ የሆኑትን ዶክተር ጎርዳን ፍሪማን አል አይን ኒውስ ጠይቋል።
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የጥናቱ መሪ ዶክተር ፍሪማን እንደገለጹት፥ አዲሱ የኮቪድ መድሃኒት የሰውነትን የበሽታ መከላከል አቅም የሚያሳድግ ሳይሆን የቫይረሱን መስፋፋት የሚገታ ነው።
የኮቪድ 19 ቫይረስ “ኤ ሲ ኢ 2” ከተሰኘው ሞሎኪዩል ማምለጥ አይችልም፥ ሞሎኪዩሉ ወደ ቫይረሱ ሲገባም የቫይረሱ የህይወት ኡደት ይገታል ነው የሚሉት ተማራማሪው።
ቫይረሱ የደቂቅ ህዋሳት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳትም እንደሚያስቆም ያብራራሉ።
መድሃኒቱ በየጊዜው የሚፈጠሩ የኮቪድ 19 ዝርያዎች ለማጥፋት እንደሚያግዝ መረጋገጡንም ነው ዶክተር ጎርደን ፍሪማን ለአል አይን ኒውስ የተናገሩት።
“ዲ ኤፍ ኮቭ 01” በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለማከም ይውላል ተብሏል።
መድሃኒቱ ወረርሽኙን አስቀድሞ ለመከላከልም ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው የዳና የካንሰር ኢንስቲትዩት የምርምር ቡድን መሪው ይናገራሉ።
የደም ግፊትን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደሌሉትም ነው የጠቆሙት።
በኮሮና በተያዙ እንሰሳት ላይ ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠው አዲስ መድሃኒት በቀጣይ በሰዎች ላይ ይሞክራል ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2023 ሙከራው ተጠናቆም ለገበያ እንደሚውል ይጠበቃል።