በቻይና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ
በአንድ ቀን ብቻ 37 ሚሊየን ሰዎች በኮቪድ 19 ሳይያዙ እንዳልቀረም ብሉምበርግ የሀገሪቱን ጤና ተቋማት አሃዞች ጠቅሶ ዘግቧል
በታህሳስ ወር 20 ቀናት ውስጥ 248 ሚሊየን ቻይናውያን በቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው ቢገምትም ቤጂንግ የምትጠቅሰው ቁጥር ከዚህ በብዙው ያነሰ ነው
ከሁለት አመት በፊት የኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘባት የቻይናው ዉሃን ከተማ ወረርሽኙ ዳግም አገርሽቶባታል።
ወረርሽኙ በታህሳስ ወር መላው ቻይናን እያዳረሰ መሆኑንም ከቤጂንግ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
ብሉምበርግ የሀገሪቱን ጤና ተቋማት አሃዞች ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ በአንድ ቀን ብቻ 37 ሚሊየን ሰዎች በኮቪድ 19 ሳይያዙ እንዳልቀረ ጠቁሟል።
በታህሳስ ወር 20 ቀናት ውስጥ 248 ሚሊየን ቻይናውያን በቫይረሱ ተጠቂ ስለመሆናቸውም ዘገባው ያክላል።
የቻይና ባለስልጣናት ግን አለም አቀፍ ጫናውን ለመቀነስ ከተጠቀሰው አሃዝ እጅግ ዝቅ ያለውን ሪፖርት እያደረጉ ነው ተብሏል።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የኮቪድ ሞቶችን የመዘገበችው ቤጂንግ በታህሳስ 22 ብቻ 4 ሺ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መኖራቸውን ይፋ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየወጡ ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሆስፒታሎች በህመምተኞች መጨናነቃቸውን የሚያሳዩ ናቸው።
የሀገሪቱ የተላላፊ በሽታዎች ተቆጣጣሪ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዣንግ ዌንሆንግ ከሻንጋዩ ዘ ፔፐር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “በቻይና የወረርሽኙ ስርጭት በአንድ ሳምንት ውስጥ ለቁጥጥር አዳጋች የሚሆንበት ደረጃ ይደርሳል” ብለዋል።
በዚህም ለከባድ ህመምና ህልፈት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቅሰው የሀገሪቱ የጤና ተቋማትም ከፍ ያለ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የአለም ጤና ድርጅትም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አሁንም የምድራችን ፈተና መሆኑን እየገለጸ ነው።
ወረርሽኙ የጠፋ የመሰላቸው በርካቶች ይሁኑ እንጂ በየሳምንቱ 10 ሺህ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ እየሞቱ መሆኑንም ነው የሚጠቅሰው።
ቻይና በፈረንጆቹ ታህሳስ 19 2019 በሁቤይ ግዛት መዲናዋ ዉሃን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተባት ወዲህ ከአለም ጤና ድርጅትም ሆነ ከምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን የሚወጡት መረጃዎች የተጋነኑ ናቸው በሚል ትሞግታለች።
ከመካሰሱ ይልቅ ቀለም ወይም ሃይማኖት የማይመርጠውን ወረርሽኝ በጋራ እንከላከለው የሚል ጥሪንም ደጋግማ ስታቀርብ ተደምጣለች።
ሃያላኑ ሀገራት በዚሁ ቫይረስ መነሻና ተያያዥ ጉዳዮች ሲነታረኩ በመላው አለም 657 ሚሊየን ሰዎችን ያጠቃው ኮሮና ከ6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
በታህሳስ ወር ዳግም በውሃን የተቀሰቀሰው ወረርሽኝም ሀገራትን ከመዘናጋት ሊያነቃቸውና የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ እንዲሰሩ ሊያተጋቸው ይገባል እየተባለ ነው።