ቻይና በትንፋሽ የሚወሰድ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ይፋ አደረገች
የቻይና የሜዲካል ምርቶች አስተዳዳሪ ክትባቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ሰጥቷል
“ካንሲኖ” በትንፋሽ የሚወሰደው ክትባት በመርፌ ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ይዘት አለው
ቻይና በትንፋሽ መልክ ወደ ውስጥ በመሳብ የሚወሰድ የኮሮና መከላከያ ክትባት ጥቅም ላይ በማዋል የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር ሆናለች።
ካንሲኖ በተባለ የቻይና ኩባንያ የተመረተው በትንፋሽ የሚወሰደው ክትባቱ በመርፌ ከሚሰጠው ክትባት ጋር ተመሳይ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ መሆኑም ተነግሯል።
ክትባቱ ከጉዳት ነጻ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በመጠቀም ሰውነታችን ኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚችልበትን መንገድ እንዲገነባ የሚያስችል ነው ተብሏል።
ካንሲኖ ኩባያ እንደስታወቀው በትንፋሽ የሚወደደው ክትባት አንድ ጊዜ ከወሰድን በኋላ ጥሩ የሆነ የመከላከል አቅም የሚሰጠን ይሆናል።
የቻይና ብሄራዊ የሜዲካል ምርቶች አስተዳዳሪ “ካንሲኖ” የተባለው በትንፋሽ የሚወሰደው የኮሮና መከላከያ በቡስተር መልክ ጥቅም ላይ አንዲውል ፈቃድ መስጠቱም ተዘግቧል።
የኮሮና ቫይረስ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ወዲህ የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፤ ተመራማሪዎች ቫይረሱን ቀድሞ መከላከል በሚቻልበት ላይ ምርምር እያደረጉ መሆኑ ይታወሳል።
በዚህም በመርፌ መልክ የሚሰጥ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ በተለያዩ ሀገራት ተሰርቶ ጥቅም ላይ እየዋል ሲሆን፤ አሁንም ምርምራቸውን መቀጠላቸው ተሰምቷል።
በዚህም የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ተመራማሪዎች በአፍንጫ ውስጥ የሚረጭ የኮሮና መከላከያ ላይ ምርመራ እና ሙከራ እያደረጉ መሆኑን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በአፍንጫ ውስጥ የሚረጨው የመከላከያ ክትባት የኮሮና ቫይረስ ወደ ሰውነታችን የሚገባበትን የአፍንጫችንን እና የላይኛውን የአየር ማስገቢያ ክፍል የበሽታ መከላከል አቅም ለማዳበር የሚረዳ መሆኑንም ተመራማሪዎቹ አመላክተዋል።