ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኮሮና ክትባቶችን አልተከተቡም መባሉ እያነጋገረ ነው
ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት ቴድሮስ አድሃኖም አልተከተቡም መባሉን አስተባብሏል
ዶ/ር ቴድሮስ እንዳልተከተቡ የሚሳዩ ናቸው በሚል የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ሃሰተኛ መሆናቸውንም ድርጅቱ አስታውቋል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኮሮና ክትባቶችን አልተከተቡም መባሉ እያነጋገረ ነው።
ዶ/ር ቴድሮስ አለመከተባቸውን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች (ቪዲዮ) ተለቀዋል።
የምስሎቹን እውነተኛነት ያጣጣለው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ አልተከተቡም መባሉን ያለ ሲሆን፤ የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ሳይቀሩ ጉዳዩን በማስተባበል ላይ መሆናቸውም ነው የተነገረው።
በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች በመዘዋወር ላይ ያለው ቪዲዮ ዶ/ር ቴድሮስ በአንድ ጆን ኮኸን በተባለ ሰው መቼ እንደተከተቡ ሲጠየቁ እና ክትባቶቹ በአፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ እስከሚደርሱ ድረስ ሳይከተቡ እንደሚቆዩ ሲናገሩ ያሳያል።
ሆኖም ቪዲዮው ሃሰተኛ ነው ሲል ድርጅታቸው አስተባብሏል። እንዲህ ዐይነቱ የፈጠራ ወሬ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አሁንም በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶችን ይጎዳል ሲልም ነው ጉዳዩን ባስተባበለበት ጽሁፉ የገለጸው።
እንደ ድርጅቱ ከሆነ ዶ/ር ቴድሮስ ባለፈው ዓመት ግንቦች ላይ የመጀመሪያውን ክትባት ወስደዋል። ከዚያም ወዲህ የማጠናከሪያ ክትባቶችን ተከትበዋል።
የድርጅት ቃል አቀባይ ጋቢ ስተርን ትናንት እሁድ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “ውሸታሞች ሲዋሹ እና ህይወትን አደጋ ላይ ሲጥሉ እርምጃ መወሰድ አለበት” ብለዋል፤ መጻፋቸው በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የተነዛውን ውሸት ለማስተባበል እንደሆነ በመጠቆም።
"ቁም ነገሩ ክትባቶች ህይወትን መታደጋቸው ነው"ም ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ዶ/ር ቴድሮስን ጠያቂው ጆን ኮኸን ዋና ዳይሬክተሩ አልተከተብኩም በሚል የተናገሩት ነገር እንደሌለ ተናግሯል።
ባሳለፍነው ሰኔ በሳይንስ መጽሄት ላይ የወጣ መጣጥፍ ዶ/ር ቴድሮስ በባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ግንቦት ላይ መከተባቸውን ያትታል።
ክትባቶች እያሉ ቀደም ብለው ለምን እንዳልተከተቡ የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ "ኢትዮጵያ ከምትባል ደሃ ሃገር እና አፍሪካ ከሚባል ደሃ አህጉር መምጣቴን አውቃለሁ፤ ስለሆነም አፍሪካ እና ሌሎች ደሃ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሃገራት ክትባቱን እስከሚያገኙ ለመጠበቅ እፈልግ ነበር" ሲሉ መመለሳቸውንም ያስቀምጣል።
በሌላ አገላለጽ ኢ-ፍትሐዊውን የክትባቶች ስርጭት በድርጊት እየተቃወሙ መሆኑንም ነው ዶ/ር ቴድሮስ የሚናገሩት።
ሆኖም አሁን በማህበራዊ ሚዲያዎች በመዘዋወር ላይ ያለው አጭር ቪዲዮ ይህን ምላሻቸውን በማካተት ከተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንታሪ) ላይ ብዙዎችን ሊያሳስት በሚችል መልኩ ተቀንጭቦ መለቀቁን ነው ተቋማቸው ያስታወቀው።