ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ለመግደል ሲዝት የነበረው ሰው ታሰረ
ተጠርጣሪው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ፕሬዝዳንቱን እንደሚገድል ከጻፈ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል
ባሳለፍነው ቅዳሜ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ መፈጸሙ ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ለመግደል ሲዝት የነበረው ሰው ታሰረ፡፡
የፊታችን ሕዳር ወር ላይ ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡
በምርጫው ላይ የዲሞክራተሮች ፓርቲ እጩ የሆኑት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ላይ የግድያ ዛቻ ሲያስተላልፍ የነበረው ተጠርጣሪ ለእስር ተዳርጓል፡፡
እንደ ኤንቢሲ ዘገባ በፍሎሪዳ ግዛት ነዋሪ የሆነው ጃሰን ፓትሪክ የተባለ የ39 ዓመት ሰው ፕሬዝዳንት ባይደንን እንደሚገድል ዝቷል፡፡
የተለያዬ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም ፕሬዝዳንት ባይደንን እንደሚገድል የዛተው ይህ ተጠርጣሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል፡፡
ጃሰን ከፕሬዝዳንት በተጨማሪም ሌሎች የተለያዩ ሀላፊዎችንም እንደሚገድል መዛቱ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ባይደን በኔቶ ስብሰባ ወቅት አዲስ ስህተት ሰሩ
ፕሬዝዳንት ባይደን በፍሎሪዳ ባለ አንድ የሕክምና ተቋም የጤና ምርመራ በማድረግ ላይ ሳሉ ግድያውን የመፈጸም እቅድ እንደነበረውም ተገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ዕለት የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ የሆኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፔንሲልቫኒያ ግዛት ለደጋፊዎቻቸው ንግግር በማድረግ ላይ እያሉ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡
ለጥቂት ከሞት ተርፈዋል የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን ህክምናቸውን ካደረጉ በኋላ በአደባባዮች ላይ ታይተዋል፡፡
የግድያ ሙከራውን አደረገው የተባለው የ20 ዓመት አሜሪካዊ ሲሆን የጸጥታ ሀይሎች በወሰዱት እርምጃ ወዲያው መገደሉ ተገልጿል፡፡