“ጠላፊው ከላካቸው ሽማግሌዎች ውስጥ የፖሊስ አዛዦች ይገኙበታል”- የጸጋ ቤተሰቦች"
“እኔን ነጻ ማውጣት አትፈልግም ወይ፤ ተደራደሩ” እያለች ነው ሲል ወንድሟ አል ዐይን አማርኛ ተናግሯል
የጸጋ ወላጅ እናትና አባት እስካሁን የልጃቸውን መጠለፍ አልሰሙም
በሀዋሳ ከአንድ ሳምንት በፊት የተጠለፈችው ጸጋ በላቸው እስካሁን ያለችበት አልታወቀም።
ጠለፋው እንዴት እንደተፈጸመና ጠላፊው ምን ፍላጎት እንዳለው አል ዐይን ቤተሰቦቹን አነጋግሯል።
በዳሽን ባንክ ሐዋሳ ዋርካ ቅርንጫፍ አካውንታት ሆና ስትሰራ የቆየችው ወይዘሪት ጸጋ፥ ማክሰኞ ግንቦት 15፣ 2015 አመሻሽ ላይ ከስራ ወደ ቤቷ ለማምራት ታክሲ የምትይዝበት ቦታ ላይ ነው የመንግስት መኪና በያዘና አስቀድሞ ለፍቅር ጓደኝነት በሚፈልጋት ግለሰብ የተጠለፈችው።
“ከቤቷ ውጭ አድራ ስለማታውቅ አከራዮቿ ወደ ጓደኞቿ እና ፍቅረኛዋ ደወሉ፤ ከዚያም እኔ ጋር ጠዋት ደውለው ጠየቁኝ” የሚለው ወንድሟ ታምሩ በላቸው፥የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ግን የጠላፊውን ስም ጠርታ የት እንደሄዱ ጭምር እንደነገረቻቸው ይገልጻል።
ጠላፊው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የአቶ ጸጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ መሆኑን መግለጿንም ያስታውሳል።
እነ ታምሩ ይህን መረጃ ይዘው ይገኙበታል ወደተባለው ይርጋለም ከተማ ከፖሊሶች ጋር ይጓዛሉ፤ ይሁን እንጂ ይርጋለም እንዳሉ “ሀገረሰላም ቡርሳ ነን” የሚል የጽሁፍ መልዕክት ደረሳቸው።
ከይርጋለም ወደ ሀገረሰላም በመጓዝም ወደ ቡርሳ የገጠር መንደር ማቅናታቸውን ነው ወንድሟ ታምሩ የሚያስታውሰው።
“በጨለማ 3 ኪሎሜትር አካባቢ በእግር ሄደን ቡርሳ ደረስን፤ የአክስቱ እና የአጎቱ ቤት ተጠቁመን አይተን ተመለስን፥ ከፖሊስ ጋር ሌሊት 10 ስአት ሄድን እስኪነጋ ጠብቀን እያንዳንዱን ቤት ፈተሽን ግን እህቴን ልናገኛት አልቻልንም። እህቴ ተግታበት የነበረው ቤት ባለቤት እና የጠላፊው የእህቱ ወንድም በቁጥጥር ስር ዋሉ” ይላል።
ጠላፊው ሀገረ ሰላም ሲገባ “እንደ ጀግና ተኩሷል” የሚለው ታምሩ፥ “እህቴንም ከአዲስ አበባ እንዳመጣትና ሊያገባት መሆኑን ሲናገርና ከጓደኞቹ ጋር ሲጨፍሩ መታየታቸውን” ከሀገረሰላም ነዋሪዎች መስማታቸውን ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጸጋ ቤተሰብ ነግረውናል።
ጸጋ በቡርሳ ለማምለጥ ሞክራ መያዟንም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሯቸው በማከል።
የጸጋ እና የጠላፊው ጥያቄ ምንድን ነው?
ጸጋ በላቸው ከተጠለፈች ስምንተኛ ቀን ቢሆናትም ድምጿን የሰማሁት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ይላል ወንድሟ ታምሩ።
“እኔን ነጻ ማውጣት አትፈልግም ወይ? እኔን ነጻ በሚያወጣ መልኩ ተደራደር” ብላኛለች፥ ይሁን እንጂ ለድርድር ከተቀመጥን ደግሞ እሷ በሰላም የምትወጣበትን ዋስትና አላገኘንም ባይ ነው።
ጠላፊው ግለሰብ ደግሞ ሽምግልና መቀመጥ ግዴታ መሆኑን ደጋግሞ መግለጹን ነው የሚናገረው። በሽምግልና የማይፈታ እና ጉዳዩን በህግ የሚይዙት ከሆነም እንደሚገላት እየዛተ ነው።
“ሊልካቸው ያሰቡ ሽማግሌዎች ደውለው አውርተውኛል፤ እስካሁን የት እንዳሉ አያውቁም፤ ደህንነቷን አላረጋገጡልኝም፤ በነሱ እጅ እንድትቆይ እንኳን ጠይቀናቸው እሽ አላሉንም፤ ተለቃ በቤተሰቦቿ ቤት ቃሏን መስጠትና ፍላጎቷን መናገር ትችላለች ስንላቸውም ይህን ማድረግ እንደማይችሉ ነገሩን” ይላል ታምሩ በላቸው።
የቤተሰቡ ጭንቀት
የጸጋ በላቸው ጠለፋ ከቤተሰቦቿ አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሆኖ መነጋገሪያነቱ ቀጥሏል።
“በዚህ ስአት እኔ እና እህቶቼ፣ የትዳር አጋሬ ትሆናለች ብሎ የሚጠብቀው እጮኛዋ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ነን” የሚለው ታምሩ፤ እናትና አባቷ እስካሁን የልጃቸውን ጠለፋ እንዳልሰሙ ነግሮናል።
“አባቴ ሆስፒታል በህክምና ላይ ነው፤ እናቴም እያስታመመችው ነው፤ በጣም የሚወዷትን ልጃቸውን ጠለፋ ከሰሙ ወላጆቼን በሞት አጣቸዋለሁ” ሲልም ስጋቱን ይገልጻል።
“እናቴ ከሰማች የፈለገው እንደሚፈጸምለት በማመን ትናንት እናታችሁን ካላገናኛችሁን ብሎ ነበር፤ አጋጣሚ ስልኳ ዝግ ስለነበር እንጂ ብታነሳው ነገር ሁሉ ይበላሽ ነበር” በማለትም የጠላፊውን የተቀነባበረ ሴራና ቤተሰቡ እያሳለፈ ያለውን የጭንቅ ጊዜ ያስረዳል።
እጮኛዋን ለማግባት እየተሰናዳች የነበረችው ጸጋ፥ ጠላፊዋ ሽማግሌ ልኮ ሚስቴ ካላደረኩሽ እያላት ነው።
በቴክስት የተለያዩ መልዕክቶችን ሲልክና ፍላጎቱን ሲገልጽ መቆየቱን የሚያወሱት ቤተሰቦቿ በዚህ ዘመን የጠለፋ ወንጀል ይፈጸማል ብለው በፍጹም እንዳልጠበቁ ይናገራሉ።
የሃዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የጸጥታ አካላ ጉዳዩን ያልሰማ የለም የሚሉት ቤተሰቦቿ፥ መረጃው እንዴት እንደሚሾልክ ባናውቅም ደብዛውን አጥፍቶ ስምንት ቀናት መቆጠራቸውን ያነሳሉ።
ጠላፊው ሊልካቸው ካሰባቸው ሽማግሌዎች ውስጥ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ከፍተኛ የስራ ድርሻ ያላቸው ግለሰብ እንደሚገኙበት በመጥቀስም፥ የህግ ያለህ እያሉ ነው ቤተሰቦቿ።
የጸጋ ቤተሰቦች ከጠላፊው ጋር ተመሳጥራ ያስጠለፈቻት ብለው የሚጠረጥሯትና በቁጥጥር ስር ውላ የነበረችው ባልደረባዋም በ30 ሺህ ብር ዋስ መውጣቷን ገልጸዋል።
የሃዋሳ ፓሊስ መግለጫ
የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ከጠለፋ ወንጀሉ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 6 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።
ፖሊስ በመግለጫው " ተጠርጣሪው ሣጅን የኋላ መብራቴ ወ/ሪት ፅጌ በላቸውን ይዞ ከተሰወረበት ቦታ አድኖ ለመያዝ ጥረትና ክትትል እየተደረገ ይገኛል "ም ነው ያለው።
አል ዐይን አማርኛ ስለጉዳዩ ለሃዋሳ ከተማ ከንቲባ እና ለከተማዋ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ተደጋጋሚ ጥያቄን ቢያቀርብም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።