ኢሰመኮ በትግራይ በ2 ወራት ውስጥ 108 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል አለ
ከሴቶች በተጨማሪም በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ህጻናት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል ኮሚሽኑ
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በትግራይ የጸጥታ ሁኔታው ያልተረጋጋ በመሆኑ የንጹሃንን ጉዳት በተሟላ መንገድ ማወቅ አለመቻሉን ገልጸዋል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ ከተወሰኑ የትግራይ ሆስፒታሎች ደርሶናል ባለው ሪፖርት “በባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 ሴቶች የአስገድዶ መድፈር”ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡
ኢሰመኮ የጥቃቱ ሪፖርት ደርሶኛል ያለው “ከመቀሌ፣ ከአይደር፣ ከአዲግራት እንዲሁም ከውቅሮ ሆስፒታሎች” ነው፡፡
የኢሰመኮ መግለጫ ከሴቶች በተጨማሪም በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ህጻናት ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል፡፡
“ኢሰመኮ በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ከፍልን በጎበኘበት ወቅት፣ ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት እና ድንጋጤ ታካሚ ሕፃናት መካከል 16ቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው” ብሏል መግለጫው፡፡
የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት ህፃናት መካከል “እጃቸውን፤እግራቸውንና አይናቸውን ጨምሮ አካላቸውን” አጥተዋል ያለው ኢሰመኮ ለጥቃቱ አንዱ ምክንያት የተቀበሩ ቦንቦች መሆኑን ኢሰመኮ ጠቅሷል፡፡
ኢሰመኮ ”ከሦስት ወራት ላለፈ ጊዜ የዘለቀው እና በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም ገና በተሟላ መልኩ ወደ መደበኛ ስራ ያልተመለሰው የመሰረት ልማት፣ የማኅበራዊ እና የአስተዳደር አገልግሎት የአካባቢውን ነዋሪዎችና እና ተፈናቃዮች ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያጋለጠ” ነው ብሏል፡፡
እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት በበርካታ የትግራይ ክልል አካባባቢዎች ባንኮች፣የጤናና የፍትህ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን ለመጀመር ተቸረዋል፡፡
“…. በመቀሌ እና የኢሰመኮ ክትትል ቡድን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በማዳረስ ረገድ አበረታች እርምጃዎች ቢኖሩም፣ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቱ አሁንም አልተሟላም።”
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንዳሉት በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ ያልተረጋጋ በመሆኑ በንጹሃን ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በተሟላ መንገድ ማወቅ አለመቻሉን መግለጫው አስነብቧል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የማጣራት ስራው እንደሚቀጥል የገለጹት ኮሚሽነር ዳንኤል በሴቶችና በህጻናት ላይ ጥቃቱ እንዳይስፋፋ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡