ሱዳን ከእስራኤል ጋር ግንኙነት መመስረት እንደምትፈልግ ይፋ አደረገች
አሜሪካ ሱዳንና እስራኤል ግንኙነት እንዲመሰርቱ እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖምፒዮ ገልጸው ነበር
ሱዳን ከእስራኤል ጋር ይፋዊ ግንኙነት መጀመር እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አስታወቀ
ሱዳን ከእስራኤል ጋር ይፋዊ ግንኙነት መጀመር እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አስታወቀ
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሌፍተናንት ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትፈልግ ይፋ አድርገዋል፡፡
ምክትል ሊቀ መንበሩ ከሀገራቸው አንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው ይህንን አስተያየት የሰጡት፡፡ ሱዳን እና እስራኤልን የተመለከተው ይህ የመሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ንግግር በከፍተኛ የሱዳን ባለሥልጣን የተሰጠ የመጀመሪያው ማብራሪያ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከእስራኤል በቀጥታ በረራ ሱዳን በሄዱበት ወቅት የሱዳንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክን ሱዳንና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጀመሩ ጠይቀዋቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ አሁን እርሳቸው የሚመሩት የሽግግር መንግስት እንጅ የተመረጠ መንግስት ባለመሆኑ ይህንን ማድረግ እንደማይችል ለማይክ ፖምፒዮ መመለሳቸውም በወቅቱ ተገልጿል፡፡
በሱዳን ፖለቲካ እጃቸው ረጅም እንደሆነ የሚጠቀሱት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ አሁን ላይ ጉዳዩን በይፋ ተናግረውታል፡፡
ካርቱምና ቴሌአቪቭ ይፋዊ ግንኙነት እንዳይጀምሩ ሲወተውቱ የነበሩት አካላት ማን ፈቅዶላቸው ይህንን እንደሚያወሩ ግልጽ እንዳልሆነ ያብራሩት ሃምዳን ዳጋሎ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ለመጀመር ሕዝቡ እንዲወስን ይደረጋል ብለዋል፡፡
እስራል በጣም ያደገች ሀገር ናት ያሉት ዳጋሎ ትልቅ አቅም ያላቸው ሀገራትም ጭምር ሁሉም ከቴላቪቭ ጋር እየሰሩ በመሆናቸው እኛም ይህንን እፈልጋለን ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡ ብዙዎች ከእስራኤል ጋር በግብርናና በቴክኖሎጂ እየሰሩ መሆናቸውንም አንስተው በግልጽ ለመናገር እስራኤልን እንፈልጋታለን ማንንም አንፈራም ስለዚህ ግንኙነቱን በዚያ መልክ አስፈላጊ እነምደሆነም አንስተዋል፡፡
በአውሮፓውያኑ 1998 በኬንያና በታንዛኒያ በሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ በተፈጸመ የሽብር ጥቃት የሱዳን መንግስት እጁ አለበት በሚል አሜሪካ ሱዳንን ሽብር ከሚደግፉ መንግስታት ተርታ መድባት ቆይታለች ፡፡ አሁን ላይ ግን የአልበሽር አገዛዝ በመውደቁ ዋሸንግተን ሱዳንን ከሽብር ዝርዝር ለማውጣት 330 ሚሊዮን ዶላር ካሳ አስልታ ጠይቃለች፡፡ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤትም ገንዘቡን ወደ ዋሸንግተን ለመላክ የአሜሪካን ዶላር በጥቁር ገበያ ጭምር እየገዛ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በዚህም የተነሳ የዶላር ዋጋ መናሩ እየተገለጸ ነው፡፡