ሚስቱን በእሳት አያይዞ የሮጠው ባል መጨረሻ
ግለሰቡ በቀጥታ ሄዶ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል

ፖሊስ በባልየው ላይ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ክስ መስርቶበታል
በምስራቃዊ ጀርመን የሚኖረው የ46 ዓመት ጎልማሳ መላው የሀገሬውን ዜጋ ያስደነገጠ ነገር ፈጽሟል፡፡
ግለሰቡ ከሚስቱ ጋር በምስራቅ ጀርመን ስር ባለችው እና ጌራ በተሰኘችው ከተማ በአነስተኛ ባቡር እየተጓዘ ነበር፡፡
ይሁንና ለጊዜው ምንነቱ ባልታወቀ ምክንያት ከጎኑ የነበረችውን ሚስቱን በእሳት አያይዞ ለማምለጥ መሞከሩን ዶቸቪሌ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ የባቡሩ ካፒቴን በእሳት የተያያዘችውን ሴት ከእሳት አደጋው በማዳን የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባት አድርጓል፡፡
የሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ቡድን በእሳት የተጎዳችውን ሴት የተሸለ ህክምና እንድታገኝ በአውሮፕላን በማሳፈር ወደ ሆስፒታል እንደወሰዳት ተገልጿል፡፡
ፖሊስ ይህን ወንጀል ፈጽሟል በሚል የጠረጠረውን ሰው ሲፈልግ ነበር የተባለ ሲሆን ተፈላጊው ሰው እጁን ሰጥቷል ተብሏል፡፡
የፖሊስ ምርመራ የቀጠለ ሲሆን እስካሁን ባልየው ሚስቱን በእሳት ለማያያዝ በምን ምክንያት እንደወሰነ አልታወቀም፡፡
በእሳት አደጋ የተጎዳችው ሚስትም ለህይወት ዘመን ህክምና ክትትል ተዳርጋለች የተባለ ሲሆን ባልየው የሚስቱን እና በባቡሩ ላይ የነበሩ ተሳፋሪዎችን ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ከባድ ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል፡፡
በባቡሩ ላይ የነበረ ሌላ ተሳፋሪ አደጋ መድረሱን ባያሳውቅ ኖሮ በሁሉም ተሳፋሪዎች ላይ የከፋ አደጋ ሊደርስ ይችል ነበር ተብሏል፡፡