በጀርመን ምርጫ የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተሸነፈ
የቀድሞው መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ሲዲዩ በ28.6 በመቶ ከፍተኛ ድምጽ ማሸነፍ ችሏል

ፓርቲው ያገኘው ድምጽ መንግስት ለመመስረት በቂ ባለመሆኑ ከአጣማሪዎች ጋር እየመከረ ነው
በ 65 ሺ የምርጫ ጣቢያዎች ከ 59 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊውን ለይቷል፡፡
በዚህም የቀድሞው መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ወግ አጥባቂው የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን (ሲዲዩ) ፓርቲ ማሸነፍ ችሏል፡፡
ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመን የተሰኘው ፓርቲ 20.8 በመቶ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት ችሏል፤ የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፓርቲ በምርጫው ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡
ምርጫው ያለጊዜው የተካሄደው ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከሶስት ፓርቲዎች ጋር የፈጠረው ጥምር መንግስት ከአንድ አመት በፊት መፍረሱን ተከትሎ ነው፡፡
ቀደም ብሎም በምርጫው ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው ሲዲዩ ፓርቲ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል በቂ ድምጽ አለማግኘቱን ተከትሎ ጥምር መንግስት ለመመስረት ከፓርቲዎች ጋር እየመከረ ነው፡፡
ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመን የተሰኘው ፓርቲ የመራሔ መንግሥት እጩ አሊስ ቫይድል በዘንድሮው ምርጫ ከፍተኛ የመራጭ ድምፅ ካገኘው ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት ለመመስረት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የክርስቲያን ዴሞክራት ህብረት መራሄ መንግሥት እጩ ፍሬደሪች ሜርዝ በአፋጣኝ መንግስት በመስረት የተሻሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለማስተዋወቅ ቃል ገብተዋል፡፡
የ69 አመቱ ሜርዝ በሚኒስትርነት ቦታ ላይ ስራ ሰርተው ባያውቁም ቀጣዩ የጀርመን መራሄ መንግስት የሚሆኑ ከሆነ አውሮፓን ለመምራት እና ለዩክሬን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
ከ1990 ወዲህ ከፍተኛ የመራጭ ተሳትፎ (83 በመቶ) መራጮች በመረጡበት ምርጫ በቅድመ ትንበያ አግኝቶት የነበረውን ከፍተኛ ግምት ተከትሎ የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ አሁን ካገኘው 28.6 በመቶ የተሻለ ድምጽ ጠብቆ ነበር፡፡
ተሰናባቹ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ የምርጫው ውጤት ለፓርቲያቸው መራራ ሽንፈት መሆኑን ገልጸው ጥምር መንግስት ለመመስረት በሚደረገው ድርድር እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።
ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን ፓርቲ ያገኘው ድምጽ ከአንድ በላይ ከሆነ ፓርቲ ጋር ጥምረት እንዲመሰርት የሚያስገድደው ነው፡፡
በዚህም ኦልተርኔቲቭ ፎር ጀርመን እና ግሪን ፓርቲ በጥምር መንግስቱ ውስጥ የመሳተፍ ከፍተኛ እድል እንዳላቸው ተነግሯል፡፡
ይሁን እና በእነዚህ ፓርቲዎች መካከል ያለው ሰፊ የርዕዮተ አለም ልዩነት ለጥምር መንግስቱ መጽናት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡