የጀርመን ህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ዛሬ ተጀምሯል
630 ወንበር ያለው የጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ውጤት የሀገሪቱ መራሄ መንግስት ማን ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል

ፍሬድሪክ ሜርዝ ለአሸናፊነት በሚጠበቁበት በዚህ ምርጫ የሩሲያ እና ትራምፕ ወዳጅ ናቸው የሚባሉት አሊስ ዋደል ከባድ ተወዳዳሪ ይሆናሉም ተብሏል
የጀርመን ህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ዛሬ ተጀምሯል
በኦላፍ ሾልዝ የሚመራው የጀርመን መንግስት ውህደት በመፈጸም መንግስት እንዲመሰረት ያደረጉ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከውህደቱ ማግለላቸውን ተከትሎ ነበር አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የተወሰነው፡፡
በዚህ ውሳኔ መሰረትም 59 ሚሊዮን ጀርመናዊያን ዛሬ ድምጽ መስጠት የጀመሩ ሲሆን ከአምስት በላይ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው የ69 ዓመቱ ፍሬድሪክ ሜርዝ ሲሆኑ ኦላፍ ሾልዝን ተክተው የጀርመን መራሄ መንግስት እንደሚሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲን የወከሉት ሜርዝ አሸናፊ እንደሚሆኑ ቢጠበቅም መንግስት መመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ላያገኙ እንደሚችሉ ተሰግቷል፡፡
ፍሬድሪክ ሜርዝ በምርጫ ወቅት ባደረገው ንግግር በህመም ላይ ያለው የጀርመንን ኢኮኖሚ እንደሚታደግ፣ የስደተኞች እና ስራ አጥ ጉዳዮችን እንደሚያስተካክልም ተናግሯል፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የቀኝ ዘመም ፓርቲ አማራጭ ለጀርመን ወይም ኤኤፍዲ የተሰኘው ፓርቲ ነው፡፡
ይህ ፓርቲ በተለይም ህይወታችንን እና ስራችንን በስደተኞች እየተቀማን ነው ብለው ከሚያስቡ ጀርመናዊያን ዋነኛ ድጋፍ ማግኘት ችሏል፡፡
የዚህ ፓርቲ መሪ የሆኑት ኢሊስ ዌደል የዶናልድ ትራምፕ አድናቂ ናቸው የተባለ ሲሆን የጀርመን ኢኮኖሚ እንዲያገግም የሩሲያን ርካሽ ነዳጅ መጠቀም አለባት ብለው እንደሚያምኑም ተገልጿል፡፡
ኢለን መስክ በይፋ ለጀርመን ችግር መፍትሔ ያመጣል በሚል ድጋፍ የተቸረው ይህ ፓርቲ ምርጫውን ካሸነፈ ጀርመን ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ይፈልጋልም ተብሏል፡፡