አዋላጅ ሐኪሞች ሚስቱን በቀዶ ጥገና ሲያዋልዱ እንዲያይ የተደረገው ባል ክስ መሰረተ
ባልየው ክስ የመሰረተው ሐኪሞች የሚስቴን ስቃይ እና ደም መፍሰስ እንዳይ በማድረግ ለአዕምሮ ህመም ዳርገውኛል በሚል ነው
ክስ የተመሰረተበት ሆስፒታልም ከባልየው ፈቃድ ውጪ ያደረኩት ነገር የለም በሚል ክሱን ውድቅ አድርጓል
አዋላጅ ሐኪሞች ሚስቱን በቀዶ ጥገና ሲያዋልዱ እንዲያይ የተደረገው ባል ክስ መሰረተ፡፡
አኔል ካፑላ የተሰኘው ሰው ከባለቤቱ ጋር ተጋብቶ የሚኖር አውስትራሊያዊ ዜግነት ያለው ሰው ነው፡፡
ትዳራቸው በልጅ መባረኩን ተከትሎ ደስታ የሞላበት ቤተሰብ እንደነበረው የሚናገረው ይህ ግለሰብ የሚስቱ መውለጃ ጊዜ ደርሶ ወደ ሜልቦርን ሆስፒታል ያመራሉ፡፡
ሐኪሞችም የሚስቱን ሁኔታ ካዩ በኋላ በቀዶ ጥገና ወይም በኦፕሬሽን ለማዋለድ መወሰናቸውን እንደነገሩት እና በአዋላጅ ሀኪሞቹ ውሳኔ መስማማቱን እንደነገራቸው ገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ህግ መሰረት ቀዶ ጥገኛ የሚያደርግ ሰው የህክምና ስራውን የቅርብ ቤተሰባቸው እንዲከታተል የመጠየቅ መብት አላቸው፡፡
ሐኪሞቹም በዚህ ህግ መሰረት ይህን ሰው የሚስቱን የማዋለድ ቀዶ ጥገና የማየት ፍላጎት እንዳለው ይጠይቁታል፡፡
ባልየውም የሐኪሞቹን ጥያቄ በደስታ መቀበሉን እና ሚስቱ በቀዶ ጥገና ስትወልድ ይመለከታል፡፡
ጤነኛ ልጃቸውን ይዘው ወደቤት ያመሩት እነዚህ ባልና ሚስት ቀስ በቀስ ግን የባልየው ጤና መታወክ ይጀምራል፡፡
እንደ ባልየው አኒል ካፑላ አስተያየት ከሆነ ሐኪሞች ሚስቱን ሲያዋልዱ የተመለከተው የአካል መቀደድ፣ መስፋት እና ደም መፍሰስ ለአዕምሮ ጭንቀት እና ድብርት ዳርጎታል፡፡
ከ3 አመት በፊት ከሞተ ባሏ የመጀመሪያ ልጇን በቅርቡ የወለደችው አውስትራሊያዊት
ይህ ሰውም አስፈሪ ቀዶ ጥገና ህክምና እንድመለከት እና ለድብርት እንድዳረግ አድርገውኛል ሲል ጉዳዩን ወደ ህግ ወስዶታል፡፡
በተፈጠረብኝ የአዕምሮ ህመም ምክንያትም ትዳሬ እንዲፈርስ ከልጄ እናት ጋርም እንዳልኖር ሆኛለሁ ሲል በሆስፒታሉ እና በሀኪሞቹ ላይ ክስ መመስረቱ ተገልጿል፡፡
ለደረሰብኝ የአዕምሮ እና ማህበራዊ ጉዳት ሜልቦርን ሆስፒታል አንድ ቢሊዮን የአውስትራሊያ ዶላር ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል ሲልም በክሱ ለይ ገልጿል፡፡
ሆስፒታሉ በበኩሉ የጣስኩት ህግ የለም፣ ክስ የመሰረተው ግለሰብ የሚስቱን ቀዶ ህክምና ማዋለድ እንዲያይ ያደረኩት በሀገሪቱ ህግ መሰረት ፈቃደኛ መሆኑን ጠይቄ ነው በሚል ክሱን ተቃውሟል፡፡
የአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ክሱን ካዳመጠ በኋላ የተጣሰ ህግ የለም፣ ክስ መስራቹ ግለሰብም ሆስፒታሉን በዚህ ጉዳይ የመክሰስ መብት የለውም ሲል መወሰኑን ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡