በአውስትራሊያ ቦታቸውን ለአልሚዎች አንሸጥም ያሉት “የዛሚት ቤተሰቦች”
አልሚዎች በሲድኒ የሚገኘውን መኖሪያቸውን በ33 ሚሊየን ዶላር ለመግዛት ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል
የዛሚት ቤተሰቦች ቦታውን ከሸጥነው “ልጆቻችን ቦርቀው የሚያድጉበት ሰፊ ቦታ አናገኝም” የሚል እምነት አላቸው
የዛሚት ቤተሰቦች የሚኖሩበት ሰፊ መንደር በአውስትራሊያዋ ሲድኒ ከተማ ውድና ታዋቂ ሆኗል።
የመኖሪያ መንደሩ ውብ እና ድንቅ የሚያደርግ ነገር ግን የለውም።
የዛሚት ቤተሰቦች መኖሪያውን ያስወደደው ለአልሚዎች የሚሊየን ዶላር የግዥ ጥያቄ እጅ ያለመስጠቱ ነው።
በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ሁሉ መሬት እየገዛ የቤት ግንባታ የጀመረው ኩባንያ ለዛሚት ቤተሰቦች 2 ሄክታር መሬት 33 ሚሊየን ዶላር ቢሰጥም ግዥውን አልተቀበሉትም።
ከላይ ሲታይ የኒውዮርክ ሴንትራል ፓርክን ይመስላልል የተባለው አረንጓዴ ግቢ የተለየ አሰራር ባላቸው ቤቶች የተከበበ ነው።
ነዋሪዎቹ ምንም እንኳን የመኖሪያ ግቢያቸው ውበት የሚደነቅ አለመሆኑን ቢያምኑም ተሽጦ ወደሌላ አካባቢ መዘዋወሩን ያልወደዱበት ምክንያት አላቸው።
የ50 አመቷ ዲያን ዛሚት፥ “ሁሉም ቤቶች የተለየ አሰራር አላቸው፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት አለ” ስትል ለዴይሊ ሜል ተናግራለች።
እናም ቤተሰቡ በቅርቡ የቀረበለትን የ33 ሚሊየን ዶላር የግዥ ጥያቄ ያልተቀበለው ተሽጦ በሚገኘው ገቢ ሰፊ ቦታ መግዛት እንደማይቻል በማመኑ ነው ብላለች።
ጎረቤቶቻቸውም “ልጆቻችን እንደልባቸው የሚቦርቁበት ብቸኛው ሰፊ ግቢ ያለው በዛሚት ቤተሰቦች መኖሪያ ነው፤ ላለመሸጥ መወሰናቸውም አስደስቶናል” ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።