በከባድ ግድያ ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ሰው ፖሊስ ሆኖ ተገኘ
ግለሰቡ ከ20 ዓመት በፊት አንድን ሰው በአደባባይ ጥይት ተኩሶ መግደሉን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተገኝቷል
መርማሪዎች ተጠርጣሪውን ለዓመታት ሲፈልጉት ቆይተው ተስፋ ቆርጠው እያለ ከሰሞኑ ድንገት በስሙ ፌስቡክ ላይ ሲፈልጉት ፖሊስ መሆኑን የሚያሳይ ምስል አጋርቶ ካዩት በኋላ ሊይዙት ችለዋል
በከባድ ግድያ ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ሰው ፖሊስ ሆኖ ተገኘ።
በፈረንጆቹ 2004 ላይ መዝናኛ ቦታ የተፈጠረ አለመግባባትን ምክንያት በማድረግ የታጠቀውን ሽጉጥ አውጥቶ ሲገድለው የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር።
ይህ ተጠርጣሪ ግድያውን በእብሪት መፈጸሙ ሳያንስ በህግ ቁጥጥር ስር አለመዋሉ የበለጠ ህዝቡን አስቆጥቶም ነበር።
ክስተቱ የተከሰተው በአሜሪካዋ ኦሂዮ ግዛት ሲንሲናቲ ከተማ ነበር።
በቅጽል ስሙ "ዳቢሎሱ" ተብሎ የሚጠራው ሰው ሙሉ ስሙ አንቶኒዮ ሪያኖ የሚባል ሜክሲኳዊ ነው።
ግለሰቡ ከ20 ዓመት ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለ ሲሆን ለትንሽ ዓመታት አድራሻ ቀይሮ ከኖረ በኋላ እስካሁን ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ከሚኖርበት አሜሪካ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሜክሲኮ ያመራል።
ይህ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ወደ ሜክሲኮ ካመራ በኋላ የሀገሪቱን ፖሊስ ተቀላቅሎ እየሰራ እንደቆየ ተገልጿል።
ከሰሞኑ የኦሂዮ ፖሊስ በወንጀል ምርመራ መዝገቡ ላይ ባለው ስሙ ፌስቡክ ላይ ሲፈልገው ተፈላጊው ሰው የሞክሲኮ ፖሊስ መለዮ ለብሶ ያጋራውን ምስል ይመለከታል።
በሁኔታው የተገረሙት ፖሊሶችም ባደረጉት ክትትል ግለሰቡ የምር እሱ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ ግድያውን ፈጽሞበታል ወደ ተባለችው ሲንሲናቲ ከተማ መጥቷል።
ተጠርጣሪው ፖሊስ የሆነው ወንጀሉን ለመደበቅ ነው ቢባልም ግለሰቡ ግን ህዝቡን ለማገልገል ስል ፖሊስ እንደሆነ ተናግሯል ሲል ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ግድያውን እንዳልፈጸመ የተናገረው ይህ ተጠርጣሪ ወንጀሉን የፈጸመበት ተንቀሳቃሽ ምስል የእድሜ ልክ እስር እንዲተላለፍበት ለማድረግ በቂ ነው ተብሏል።