ሲም ካርድ በመቀየር ስለሚሰራው የማጭበርበር ወንጀል ምን ያህል ያውቃሉ?
ወንጀሉ የሰዎችን ስልክ ቁጥር የራስ በማስመሰል የባንክ እና ሌሎች የፋይናንስ መረጃዎችን መስረቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው
ከ2018 እስከ 2021 በዚሁ ወንጀል ምክንያት 68 ሚሊየን ዶላር ከሰዎች የግል ሂሳብ ተዘርፏል
ኢሜይል እና የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ከሚቃጣው የሳይበር ጥቃት ባለፈ የሰዎችን የስልክ ቁጥር የራስ በማስመሰል የሚሰሩ የማጭበርበር ወንጀሎች እየበረከቱ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡
ይህን ስራ የሚሰሩት አጭበርባሪዎች የሰዎችን ስልክ ቁጥር የራሳቸው እንደሆነ በማስመሰል ወደ ቴሌኮም ኩባንያ በመደወል ስልካቸው እንደተሰረቀ ወይም እንደተበላሸ በመንገር ስልክ ቁጥሩን በራሳቸው ካዞሩ በኋላ የሰዎችን ገንዘብ እና ግላዊ ሚስጥሮች ይመነትፋሉ።
የስልክ ቁጥሩ ባለቤት ስልኩ እጁ ላይ እያለ የሚደወሉ ስልኮች እና መልዕክቶች በአጭበርባሪዎቹ እጅ የሚገባ ሲሆን ቀጥሎም የባንክ እና ዲጂታል መገበያያ መተግበርያ የይለፍ ቃሎችን በመቀየር አጭበርባሪዎቹ ያሻቸውን ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።
ወንጀለኞቹ ድርጊቱን ከመፈጸማቸው በፊት የግል ተበዳዩን የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፣ ኢሜል መልዕክት እና የማህበራዊ ዋስትና መረጃዎችን ቀደም ብለው የሚያሰባስቡ ሲሆን፤ ስልክ ቁጥሩን ወደ ራሳቸው ለማዞር ሲሞክሩ በቴሌኮም ኩባንያዎች ለሚጠየቁት ሚስጥራዊ ጥያቄዎች ከስልክ ቁጥሩ ትክክለኛ ባለቤት በዚህ መንገድ ያሰባሰቡትን መረጃ ይጠቀማሉ፡፡
ቀላል እና አንድ አይነት የይለፍ ቃል ለተለያዩ የፋይናንስ እና የባንክ መተግበርያዎች የሚጠቀሙ ሰዎች ለዚህ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) የኢንተርኔት ወንጀሎች ክፍል ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚቀርቡለት ጥቆማዎች ከ2018 እስከ 2021 በ400 እጥፍ መጨመራቸውን ያሳወቀ ሲሆን ከ68 ሚሊየን ዶላር በላይ በዚሁ ወንጀል ምክንያት መዘረፉን ይፋ አድርጓል፡፡
ከገንዘብ ስርቆቱ ባለፈ ወንጀል ፈጻሚዎቹ የተበዳዩን የግል ሚስጥሮች ከማህበራዊ ትስስር ገጾች፣ ከጽሁፍ እና ድምጽ መልእክቶች ላይ በመውሰድ ገንዘብ እንዲከፈላቸው ካልሆነ የግል መረጃውን እንደሚያጋልጡ በማስፈራራት ገንዘብ እንደሚቀበሉም ተደርሶበታል፡፡
ኤፍቢአይ ወንጀሉን ለመከላከል ሰዎች ለተለያዩ መተግበርያዎች የሚጠቀሟቸውን የይለፍ ቃሎች አንድ አይነት አለማድረግ ፣ ለማያውቁት ሰው የስልክ መረጃቸውን ከመስጠት መቆጠብ ፣ የሚጠቀሟቸውን የይለፍ ቃሎች በተቻለ መጠን ጠንከር እንዲሉ ማድረግ ፣ የኢንተርኔት ፋይናንስ አገልግሎት እና የገንዘብ እንቅስቃሴያቸውን በቅርበት መከታተል እንደሚገባ መክሯል፡፡
ለየት ያለ እና ያልተለመደ የፋይናንስ እንቅስቃሴ በሚመለከቱ ጊዜም ወደ ቴሌኮም እና ፋይናንስ ተቋማት በፍጥነት በማሳወቅ ወንጀሉን መከላከል ይችላሉ ነው የተባለው፡፡