አሜሪካ በተለያየ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከጎረቤት ኬንያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር ተወያይታለች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ከእኛ ጋር በቀጥታ ከመወያየት ይልቅ ከሌሎች ሀገራት ጋር መወያየትን መርጣለች ብለዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር መወያየታቸው ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጀፍሪ ፊልትማን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከቱርክ፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና ግብጽ ጋር መክረዋል ብለዋል አምባሳደር ዲና።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ መወያየት ከፈለለገች እኛ ሁሌም ዝግጁ ነን የሚሉት አምባሳደር ዲና በእኛ ጉዳይ ከእኛ ጋር መወያየት አለባቸውም ብለዋል።
በተጠናቀቀው የፈረንጆች 2021 ዓመት ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተነዙ ሀሰተኛ ሙረጃዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው የተለያዩ አቋም የያዙ አገራት እና ተቋማት የታዩበት ዓመት እንደነበርም አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው ላይ ገልጸዋል።
በአዲሱ 2022 ዓመት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ በአዲስ መንገድ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እንደምትሰራም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት እና ሌሎች ምክንያቶችን ታሳቢ አድርገው ከእኛ ጎን ያልቆሙ ሀገራትን እና ተቋማትን ሳናኮርፍ ፍላጎታችንን ተረድተው ከእኛ ጎን እንዲቆሙ በአዲሱ ዓመት እንደሚሰሩ አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
አሜሪካ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ከቀረጽና ኮታ ነጻ የንግድ ችሮታ(አጎአ) መሰረዟ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔው ተራ ዜጎችን እንደሚጎዳና አሜሪካም ውሳኔውን እንድትቀለብስ ቢጠይቅም፤ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔውን ሊቀለብስ አልቻለም፡፡