አሜሪካ ገንዘብ ሌላቸው ዜጎቿ የጉዞ ቲኬት መግዣ ብድር አመቻችታለች
አሜሪካ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ ለ17ኛ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሰጠች፡፡
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ በህወሓት መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።
ይሄንን ተከትሎም ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከመፈረጁ በፊት የሀገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ለመውሰድ ወደ ትግራይ ክልል ከገባ ከስምንት ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አውጆ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መመለሱም አይዘነጋም።
ከዚህ ውሳኔ በኋላም ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች አዲስ ጥቃት የከፈተ ሲሆን በተለያዩ የውጊያ ግምባሮች ጥቃቶችን ከፍቶ በርካቶችን በማፈናቀል ንብረት እና መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።
ህወሓት በተለይም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ያሉትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ አሜሪካ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ አሳስባለች።
ሀገሪቱ ማስጠንቀቂያውን ያወጣችው ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በመሆኗ የጸጥታ ሁኔታው አስጊ ነው በሚል ነው፡፡
የገንዘብ ችግር ያለባቸው አሜሪካዊያን የጉዞ ቲኬት በብድር እንዲገዙም አሰራር መዘርጋቷን አዲስ አበባ ባለው ኢምባሲዋ ድረገጽ በኩል አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ ከህዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ እስከ ዛሬ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ 17 ጊዜ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች።
በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ አሜሪካዊያን አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ በምክንያትነት በማሳሰቢያው ላይ ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ዜጎች የጉዞ ቲኬት መግዣ የገንዘብ ችግር ከገጠማቸው ብድር መዘጋጀቱንም በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎቹ ላይ ጠቅሷል።
በተጨማሪም አሜሪካ በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ስለሚችል ዜጎቿ ወደ ገበያ ማእከላት እና ህዝብ ወደ ሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ከመሄድ እንዲቆጠቡ አሳስባ እንደነበረም አይዘነጋም።
በአስቸኳይ ኢትዮጵያን ለቀው ይውጡ የሚለው የአሜሪካ ተደጋጋሚ ማሳሳቢያ በኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ ገጥሞታል።
የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ጸጥታ አስመልክቶ የሚያወጣውን መግለጫ እንዲያቆም ማሳሰቡ ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በየዕለቱ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የሚያርጉት በረራ የጨመረ ሲሆን ተጓዦች የጉዞ ቲኬት ለማግኘት ችግር ላይ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
አልዓይን ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ወዳሉ የጉዞ ቲኬት መሸጫ ማዕከላት በመሄድ ባደረገው ማጣራት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስከ ፈረንጆቹ ጥር 10 ቀን 2022 ድረስ ከቢዝነስ ክላስ ውጪ ያሉ የጉዞ ቲኬቶች ተሸጠው አልቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በመቀጠል ከአሜሪካ እና አውሮፓ አውሮፕላን ጣቢያዎች መንገደኞችን ወደ አዲስ አበባ የሚያመጣው የተባበሩት አረብ ኢምሬት አየር መንገዶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የጉዞ እገዳ መጣላቸው ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡ መንገደኞች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረሱንም ከጉዞ ቲኬት ሻጮች ሰምተናል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸውን ካሳወቁ በኋላ ህወሃት ይዟቸው የነበሩት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉና ከምስራቅ አማራ ማስወጣቱን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡ መንግስት ጦርነቱን ማሸነፉን ቢናገርም ህወሓት ግን ለሰላም ሲባል ከአፋርና አማራ ክልሎች መውጣቱን ገልጾ ነበር፡፡