በዩክሬን እና ፖላንድ ድንበር የወደቀው ሚሳይል ኔቶ በብራሰልስ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ምክንያት ሆኗል
በምስራቃዊ ፖላንድ የወደቀው ሚሳይል ጉዳይ ከዋርሳው እስከ ኢንዶኔዥያዋ ባሊ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።
ፖላንድ ከዩክሬን በሚያዋስናት ድንበር ወድቆ ሁለት ሰዎችን የገደለው ሚሳይል ሩስያ ስራሽ መሆኑን ገልፃለች።
የፖላንዱ ፕሬዚዳንት አንድሬዥ ዱዳ የሚሳይሉ ስሪት ከሩስያ መሆኑ ለእውነት የተቃረበ መሆኑንና መነሻውም እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኸባድ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን ፤ የማጣራት ስራውም ቀጥሏል ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዜሌንስኪም የሞስኮ ፀብ አጫሪ ድርጊት የአአካቢውን ውጥረት ያንረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።
በኢንዶኔዥያ ባሊ በቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግን ሚሳይሉ ከሩስያ የተወነጨፈ አይመስለኝም ብለዋል።
ባይደን ከዋርሳውና ኬቭ ብቻም ሳይሆን ከሀገራቸው ፓለቲከኞችም ጭምር በተቃርኖ የሰጡት አስተያየት ነገሩን ረገብ አድርጎታል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን ለአሶሼትድ ፕረስ በሰጡት አስተያየት ከሩስያ የተወነጨፈ ሚሳኤል ፖላንድ መውደቁን ተናግረው ነበር።
የሚሳኤሉ ስሪት የሩሲያ መሆኑ በስፋት ቢነገርም መነሻውን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች እየወጡ ነው፤ የኤፒ ዘገባ ሚሳኤሉ ከዩክሬን የተወነጨፈ ሊሆን ይችላል ብሏል።
በፓላንድ የወደቀው ሚሳኤል 30 የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ላይ እንደተቃጣ ነው የሚቆጠረው።
ፖላንድም ሆነች ኔቶ ግን እስካሁን ሩስያ ጥቃቱን ሆን ብላ ፈፅማዋለች የሚል መግለጫ አላወጡም።የኔቶ ዋና ፀሃፊ የንስ ስቶተንበርግ በብራሰልስ የጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የሚያሳልፉት ውሳኔ ይጠበቃል።
የፀጥታው ምክር ቤትም በዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመምከር አስቀድሞ ለዛሬ በያዘው ቀጠሮ የፖላንድን ስጋት ይመለከታል ተብሏል። ሩሲያ በበኩሏ ከደሙ ንፁህ ነኝ የሚል መግለጫ ማውጣቱን ሬውተርስ አስነብቧል።