ተመድ እና ሩሲያ በጥቁር ባህር በኩል ምርቶችን ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ምክክር አደረጉ
በዩክሬን ወደቦች የተከማቸ ስንዴ ለአለም ገበያ እንዲቀርብ የተደረሰው ስምምነት ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ ሰባት ቀናት ቀርተውታል
ሩሲያ ስምምነቱ እንዲታደስ ፈቃደኝነቷን ካላሳየች የአለም አቀፉ የምግብ ዋጋ ተጨማሪ ቀውስ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል ተብሏል
የመንግስታቱ ድርጅት እና የሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በጥቁር ባህር በኩል ምርቶችን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማቅረብ የሚያስችል ምክክር በጄኔቫ አደርገዋል።
ሞስኮ ክሬሚያ ላይ በዩክሬን ተቃጣብኝ ካለችው ጥቃት በኋላ በጥቁር ባህር በኩል የዩክሬን ምርቶች ለአለም አቀፍ ገበያ ከሚቀርብበት ስምምነት እወጣለሁ ማለቷ ይታወሳል።
ኬቭ በበኩሏ ለጥቃቱ ሃላፊነት አልወሸደችም፤ ለስንዴ መተላለፊያ የተፈቀደን መስመር ለወታደራዊ ግልጋሎትም አላዋልኩትም ብላለች።
የተቋረጠውን የዩክሬን የስንዴ የወጪ ንግድ ለማስጀመር የሚያስችል ምክክር በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሂዷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ እና አስቸኳይ የምግብ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ እና የአሜሪካ የንግድ ሬቢካ ግሬይንፓን ከሩስያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰረጌ ቬርሽኒን ናቸው ምክክሩን ያደረጉት።
ከውይይቱ በኋላም በሀምሌ ወር የተደረሰው ስምምነት እንዲቀጥል ገንቢ ምክክር መደረጉን የመንግስታቱ ድርጅት ያወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ሩሲያ ምግብና ማዳበሪያ ያለምንም ገደብ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንድትችል በተጀመረው ንግግር ዙሪያም ውይይት መደረጉ ተነስቷል።
የመንግስታቱ ድርጅት እየናረ የመጣውን የማዳበሪያ ዋጋ ለማረጋጋት ጥረት እንደሚያደርግ በመግለጫው መጥቀሱን ሬውተርስ አስነብቧል።
ስምንት ወራት ያለፉት የዩክሬን ሩስያ ጦርነት በአለም አቀፍ የምግብ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል።
ቱርክ እና የመንግስታቱ ድርጅት በመሩት ድርድርም በዩክሬን ወደቦች የተከማቸ ስንዴ ለአለም ገበያ እየቀረበ ነው።
ይህ ስምምነት ሊጠናቀቅ ግን ሰባት ቀናት ብቻ ነው የቀሩት።
ሩሲያ ስምምነቱ እንዲታደስ ፈቃደኝነቷን ካላሳየች የአለም አቀፉ የምግብ ዋጋ ተጨማሪ ቀውስ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል ተብሏል።