ሩሲያ የወጪ መጠባበቂያ በጀቷን ወደ 547 ቢሊዮን ዶላር ከፍ አደረገች
ሞስኮ የመጠባበቂያ በጀቷን ከፍ ያደረገችው በተጣሉባት ማዕቀቦች ኢኮኖሚዋ እንዳይጎዳ በሚል ነው
ሩሲያ በአሜሪካ እና አውሮፓ የነበራት የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ገንዘብ መታገዱ ይታወሳል
ሩሲያ የመጠባበቂያ በጀቷን ወደ 547 ቢሊዮን ዶላር ከፍ አደረገች፡፡
ዩክሬን ወደ ሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ወደ ጦርነት ያመሩ ሲሆን ይህ ጦርነት ዘጠን ወራት ሞልቶታል፡፡
ለልዩ ዘመቻ በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን የላከችው ሩሲያ ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል፡፡
ሩሲያም ወዳጅ አይደሉም ባለቻቸው ሀገራት ላይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን የወሰደች ሲሆን ከአውሮፓ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ብልሽት ገጥሞታል፡፡
ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚዋ እንዳይጎዳ በሚል የመጠባበቂያ ውጭ ምንዛሬ በጀቷን ወደ 547 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማድረጓን አርቲ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት በተጀመረበት ባሳለፍነው የካቲት ወር ላይ የሞስኮ ብሄራዊ የውጭ መጠባበቂያ ገንዘቧ 643 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን ይህ አሀዝ አሁን ላይ የ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል፡፡
የሩሲያ ማዕከላዊ ባክ እንዳለው የሞስኮ ኢኮኖሚ በአወንታዊ ሂደት ውስጥ እንደሆነ ገልጾ የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ መጠን ጭማሪ የተደረገው ኢኮኖሚው እያደገ መሆኑን ተከትሎ መሆኑንም አክሏል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ማምራቷን ተከትሎ በውጭ ሀገራት ያስቀመጠቻቸው ገንዘቧ የተያዘባት ሲሆን የህ የታገደው ገንዘብ የሀገሪቱን ብሄራዊ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ግማሹ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ቀሪው ደግሞ በወርቅ እና በቻይና ዩዋን መልክ በሀገር ውስጥ እና በሌሎች ሀገራት ባንኮች ውስጥ እንዳለ ዘገባው አክሏል፡፡
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት እንድታቆም የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ሲሆኑ ከነዚህ መካከልም የሩሲያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ለይ እንዳይቀርቡ ማዕቀቦችን መጣል ዋነኛው ነው፡፡
ይሁንና ቻይና፣ ህንድ ፣ተርኪየ፣ እና ሌሎች ሰፊ ህዝብ እና ፍላጎት ያላቸው ሀገራት የሩሲያ ምርቶችን በመግዛት ላይ ናቸው፡፡