ባይደን ከእስያ የአሜሪካ አጋሮቻ ጋር ለመምከር ካምቦዲያ ገብተዋል
ፕሬዚዳንቱ ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂምፒንግ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በፕኖምፔን ፊት ለፊት ይገናኛሉ
የባይደን ጉዞ አሜሪካ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ያላትን ፍላጎት ለማሳካት የእስያ አጋሮቿን ትብብር ማስፋትን አላማ ያደረገ ነው ተብሏል
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ካምቦዲያ ገብተዋል።
ባይደን በደቡብ ምስራቅ የእስያ ሀገራት ማህበር ጉባኤ ለመሳተፍ ነው ካምቦዲያ ፕኖም ፔን የደረሱት።
የፕሬዚዳንቱ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን፥ የባይደን ጉዞ አሜሪካ በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና ያላትን ፍላጎት ለማሳካት የእስያ አጋሮቿን ትብብር ማስፋትን አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
ባለፈው አመት ይፋ የተደረገው የኢንዶ ፓስፊክ የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ እና የደህንነት አጋርነትን የተመለከቱ ምክክሮችም ከአስሩ የደቡብ ምስራቅ የእስያ ሀገራት ማህበር መሪዎች ጋር ይደረጋሉ ነው ያሉት።
ባይደን ሀገራቱ በኢንዶ ፓስፊክ ህገወጥ የባህር ላይ ጉዞ እና የአሳ ማስገርን ለመቆጣጠር የሳተላይት ምስሎችን የሚለዋወጡበትን ስርአትም ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የካምቦዲያ ጉዞ ቤጂንግ ላይ ያነጣጠረ ይመስላል።
ፕሬዚዳንቱ በኢንዶኔዥያ ከሚደረገው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ ጎን ለጎን ከቻይናው አቻቸው ሺ ጂምፒንግ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።
ባይደን ኋይትሀውስ ከገቡ ወዲህ ከሺ ጂምፒንግ ጋር አምስት ጊዜ የስልክ ውይይት አድርገዋል፤ በስልጣን ዘመናቸው ፊት ለፊት ሲገናኙ ግን የፊታችን ሰኞ የመጀመሪያቸው ይሆናል።
የውይይታቸው አንኳር ነጥቦች መካከልም በኢንዶ ፓስፊክ ቀጠና የቤጂንግን ተፅዕኖ መግታት የሚለው አንዱ ነው።የንግድም ሆነ የፓለቲካ ልዕለ ሀያልነትን ለመጨበጥ 60 በመቶ የአለም ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) እና 50 በመቶ የአለም ሸቀጥ መተላለፊያውን የኢንዶ ፓስፊክ መቆጣጠር ወሳኝ ድርሻ አለው።
ቻይና ሰው ሰራሽ ደሴቶችን ጭምር እየገነባች መስፋፋትን ይዛለች የምትለው አሜሪካ፥ በርካታ ዘመናዊ የጦር መርከቦቿን አሰማርታለች።
እንደ ህንድ ያሉ የእስያ ሀገራትን አጋር በማድረግም ቤጂንግን ለማስቆም ያስችላሉ ያለቻቸውን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች እያደረገች ነው።
ካምቦዲያ የገቡት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ከሺ ጂንፒንግ ጋር ከመምከራቸው በፊት አጋሮቻቸውን አስቀድመዋል።
ባይደን በፕኖም ፔን ቆይታቸው ከጃፓንና ደቡብ ኮሪያ መሪዎች ጋር ይወያያሉ።
በቅርቡ ወደ ሁለቱም ሀገራት ሚሳኤል አስወንጭፋለች የተባለችው ሰሜን ኮሪያም የምክክሩ ዋነኛ ርዕስ ትሆናለች ብለዋል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫን።
በፈረንጆቹ 2021 ስምንት ጊዜ የባለስቲክ መሳሪያ የተሞከረችው ፒዬንግያንግ፥ ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት በቀረው 2022 ወደ 32 እንዳሳደገችው ተነግሯል።
ይህም ሀገሪቱ የኒዩክሌር መሳሪያን ጥቅም ላይ ለማዋል መሰናዳቷን ያሳያል የሚሉ የአሜሪካ ባለስልጣናት፥ የፒዬንግያንግ ከጋር የሆነችው ቻይና ጫና እንድታደርግ እየጠየቁ ነው።
ፕሬዚዳንት ባይደንም በኢንዶኔዥያ ባሊ ከሺ ጂንፒንግ ጋር ሲወያዩ የሰሜን ኮሪያ ጉዳይም ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ጃክ ሱሊቫን አረጋግጠዋል።