ፕሬዝዳንት ባይደን፤ “በቻይና በኩል ታይዋንን ለመውረር ምንም ዓይነት የቅርብ ጊዜ እቅድ ያለ አይመስለኝም” አሉ
ጆ ባይደን፤ ቻይና በታይዋን ላይ የፈጸመችው “አስጨናቂ” እርምጃ ሰላምን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል
የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ የታይዋን ጉዳይ ሊጣስ የማይገባው “ቀይ መስመር ነው” ብለዋል
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ በታይዋን ላይ “በቅርቡ ጥቃት ለመሰንዘር አቅደዋል” የሚል እምነት የለኝም አሉ፡፡
ባይደን ይህን ያሉት በዋሽንግተን እና ቤጂንግ መካከል እያሽቆለቆለ የመጣውን ግንኙነት ያድሳል በተባለለትና ከኢንዶኔዢያው የቡድን-20 ጉባኤ ጎን ለጎን በአካል ተገናኝተው ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
“በቻይና በኩል ታይዋንን ለመውረር ምንም ዓይነት የቅርብ ጊዜ እቅድ ያለ አይመስለኝም” ብለዋል ፕሬዝዳንት ባይደን፡፡
ፕሬዝደንቱ አክለውም "አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት መኖር እንደሌለበት ሙሉ በሙሉ አምናለሁ" ብለዋል፡፡
ባይደን በአካል ስላገኘዋቸውና ለሶስት ሰአታት ያክል ለውይይት አብሮዋቸው ስለተቀመጡት የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ሲናገሩም ዢ ቀደም ብየ (በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባማ የስልጣን ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት ሳሉ) የማውቀው ሰው አይንት ሆኖ ነው ያገኘሁት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“በጣም ተከራካሪ ወይም ለዘብተኛ ሆኖ አላገኘሁትም። እሱ ሁልጊዜ እንደነበረው ግልጽ እና ቀጥተኛ ሆኖ ነው ያገኘሁት” ሱሉም ነው ዢን የገለጿቸው፡፡
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው ፤ ባይደንን በታይዋን ደሴት ጉዳይ የቤጂንግን "ቀይ መስመር" እንዳያለፉ ማስጠንቀቃቸው የመንግስት የዜና ወኪል ሺንዋ ዘግቧል ።
ዢ “የታይዋን ጉዳይ የቻይናን ዋና ፍላጎት እንዲሁም ለቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት ፖለቲካዊ መሰረት እንደመሆኑ በቻይና-አሜሪካ ግንኙነት መጣስ የሌለበት የመጀመሪያው ቀይ መስመር ነው” ሲሉ ተናገረዋል፡፡
የቻይናው መሪ ዢ ይህን ይበሉ እንጅ የአሜሪካው አቻቸው ባይደን ግን ቻይና በታይዋን ላይ የፈጸመችው “አስጨናቂ” እርምጃ ሰላምን አደጋ ላይ እንደሚጥል ለ ዢ ገልጿል።
ጆ-ባይደን የቻይና ድርጊት “በታይዋን የባህር ዳርቻ እና በሰፊው ቀጠና ሰላም እና መረጋጋትን ያበላሻል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የዋስንግተን እና የቤጂንግ ግንኙነት በተለይም የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋንን ጉብኝት ተከትሎ ሲሰነዘሩ በነበሩ ዛቻዎች እጅግ እየተካረረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡እናም የአሁኑ የመሪዎቹ መገናኘት ታይዋንን ሽፋን በማድረግ ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ያረግበዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡