ከ600 በላይ ኢትዮጵያውያን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ከሊባኖስ እንደሚመለሱ መንግስት አስታውቋል
ከ600 በላይ ኢትዮጵያውያን በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ከሊባኖስ እንደሚመለሱ መንግስት አስታውቋል
በሊባኖስ በቤት ውስጥ ስራ ተሰማርተው ከሚገኙት ስደተኞች የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛው መሆኑን የሃገሪቱ ስደተኞች ጉዳይ መስርያ ቤት በፈረንጆቹ 2018 ባወጣው መረጀ አስታውቋል፡፡
ሊባኖስ በኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ከ7 ወር በፊት ባጋጠማት የፖለቲካ ችግር ምክንያት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ለቀውስ ተዳርጓል፡፡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም የዚህ ችግር ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ ሀገሪቱ ባጋጠማት ችግር የተነሳ አሰሪዎች በበቂ መጠን የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ባለመቻላቸው በቤት ውስጥም ሆነ በድርጅቶች የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ክፍያ ባለማግኘት አሊያም ክፍያቸው በመቀነሱ ለችግር ስለመዳረጋቸው አንስተዋል፡፡
ቅሬታቸውን ለአል ዐይን የተናገሩት ኢትዮጵያውያኑ “ነገ ይከፈለኛል” በሚል ተስፋ ያለ ደሞዝ እንዲሰሩ ስለመገደዳቸው፣ በቤት ውስጥ የሚሰሩት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ባለመኖሩ ደሞዝ ሳይከፈላቸው ከ 7 ወራት በላይ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በሀገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ላይ አሁን ዓለምን እየፈተነ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ ሲጨመር ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ እየገጠማቸው ያለው ችግር ውስብስብ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገራት ስደተኞች ያለስራ ቤታቸው ለመቀመጥ መገደዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ከ7 ወራት በላይ በዘለቀው የአገሪቱ ቀውስ እና አሁን በመጣው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለጥንቃቄ ሲባል በሊባኖስ መንግስት በታወጀው የመንቀሳቀስ ገደብ ምክንያት ወጥቶ መስራት እና መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሆኗልም ተብሏል፡፡ በመሆኑም ለቤት ኪራይ፣ለ ምግብና ለህክምና ችግር መጋለጣቸውን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ባለው ችግር ምክንያት በአንድ ቤት ውስጥ እስከ 14 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ለመኖር ስለመገደዳቸው ያነሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ዜጎች ከዚህ ለከፋ ችግር ከመጋለጣቸው አስቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት ከሊባኖስ መንግስት ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑን ከሊባኖስ ስለመመለስ የመንግስትን አቋም የጠየቅናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ቃል አቀባይ አምሳሉ ትዕዛዙ ፣ መንግስት በሊባኖስ ችግር ላይ ያሉ ዜጎችን በሚመለከት ከሀገሪቱ መንግስት ጋር እየሰራ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
አቶ አምሳሉ ትዕዛዙ
ተጠባበቂ ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያውያኑ በሀገሪቱ ለቆዩበት ክፍያ (ቀራማ ክፍያ) እንዲከፍሉ የሚጠየቅ ቢሆንም በሀገሪቱ ያለው ቆንጽላና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሀገሪቱ ደህንነትና ስደተኞች ጉዳይ ጋር በመተባበር እንዲቀር ተደርጓል ብለዋል፡፡ከዚህ ስምምነት አስቀድሞ ግን ክፍያውን እንዲከፍሉ እንደሚገደዱና ይህንን ካላደረጉ ግን ለእስር ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ከሊባኖስ ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡ 624 ዜጎች በጥቂት ቀናት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የተገለጸ ሲሆን የትራንስፖርት ሁኔታው ላይ ውይይት እንደሚደረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እየተከታተሉት መሆኑንም አቶ አምሳሉ ገልጸዋል፡፡