በአማራ ክልል 4ሺ 813 ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ነው-የዞኑ ፖሊስ መምሪያ
በአማራ ክልል 4ሺ 813 ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተካሄደበት ነው-የዞኑ ፖሊስ መምሪያ
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በአይሱዙ ጭኖ ሲጓዝ የነበረ አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የመምሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዓባይ አሻግሬ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ተሽከርካሪው ገንዳውኃ ከተማ መግቢያ ኬላ ላይ ሲደርስ በተደረገ ፍተሻ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ጭኖ ተገኝተውበታል ብለዋል፡፡
ኢንስፔክተር ዓባይ እንደገጹት ተሽከርካሪው ሲፈተሽ 289 የቱርክ ሽጉጥ፣ 4ሺ 337 የቱርክ ሽጉጥ ጥይት እና 185 የብሬን ጥይቶች ተገኝተዋል፡፡
ህገ-ወጥ መሳሪያዎቹ በተሽከርካሪዉ የመጫኛ ወለል ስፖንዳ ላይ በተበየደ ተጨማሪ ስፖንዳ የተጫኑ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በክልሉ ልዩ ኃይል አባላት አማካኝነት በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብሏል፡፡
በፍተሻ የተገኙት የጦር መሳሪያዎች ብዛት 4ሺ 813 መሆናቸውን ፓሊስ ገልጿል፡፡
“ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የኢትዮጵያ ሰላም”በሚል ርእስ ባለፈው የካቲት 6፣2012 ዓ.ም በአዲስ አባባ በተካሄደ ውይይት ላይ የፌደራል ፖሊስ ከሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ህገወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥር መጨመሩን ገልጾ ነበር፡፡
በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ የህግ አገልግሎት ዳይሬክትር ኮማንደር ፋሲለ አሻግሬ እንደገለጹት በግማሽ ዓመት ብቻ 2118 ክላሽ ፣ 28ሺ698 የክላሽ ጥይት፣ 6823 ሽጉጦች፣ 140 ሺ 353 የሽጉጥ ጥይት፣ 362 ከባድና ቀላል የጦር መሳሪያዎች 93ሺ 115፣ የከባድና ቀላል የጦር መሳሪያዎች ጥይቶች እና 40 ቦምቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት በሚያዋስኗት የድንበር ቦታዎች ላይ ባለው የላላ ቁጥጥር ምክንያት፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች በሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በጅቡቲ፣በኬንያ በኩል በገፍ እየገቡ እንደሆነና ይሄም በሀገርውስጥ ሰላም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳላቸው መንግስት ገልጿል፡፡
እንደ ፌደራል ፖሊስ ሪፖርት ከህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 583 ወንጀሎች ተሰርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዋጅም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል፡፡