ነገና ከነገ በስቲያ በርከት ያሉ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብራቸውን ያካሄዳሉ
ምርጫው 4 ቀናት እስከሚቀሩት ድረስ የሚዘልቀው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ባሳለፍነው ሰኞ በይፋ መጀመሩም የሚታወስ ነው
አብን፣ ባልደራስ፣ ኢዜማ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ይህንኑ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል
በ6ኛው ሐገር አቀፍ ምርጫ የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው የተሻለ ተሳትፎ ለማድረግ ያስችለናል ያሉትን የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እያካሄዱ ነው፡፡
በምርጫው በተሻለ ቁመና ላይ ተገኝቶ አሸናፊ ለመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወንኩ እገኛለሁ ያለው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ከነገ በስቲያ እሁድ የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ አብሮ ለመስራት ከተስማማቸው ፓርቲዎች ጋር በመሆን የጋራ የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደሚኖረው አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ ዕለት በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደሚኖረውም ነው አብን ያስታወቀው፡፡
መርሃ ግብሩ የአደባባይ ትዕይንቶችን እና ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ትርዒቶችን እንደሚያካትትም ገልጿል፡፡
አብን ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ)፣ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ) ጋር አብሮ ለመስራት ያስችለኛል ያለውን ጥምረት እንደፈጠረ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
ከአሁን ቀደም ሊያደርጋቸው የነበሩ ሰልፎችን የተከለከለው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ከየካቲት 14 -16 ቀን 2013 ዓ/ም የሚዘልቅ የምርጫ ቅስቀሳ የመክፈቻ ስነ ስርዓት አዘጋጅቻለሁ ብሏል በይፋዊ የማህበራዊ ገጹ ባሰፈረው መግለጫ፡፡
መነሻውን 6 ኪሎ ከሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ የሚያደርገው የቅስቀሳ ስነ ስርዓቱ በማርሽ ባንድ እና ሌሎችም ትዕይንነቶች እንደሚታጀብም ባልደራስ አስታውቋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ የመጀመሪያ የፓርቲ ኮንፈረንሱን በማድረግ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ም ነገ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2013 ዓ/ም የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ያካሂዳል፡፡
መርሃ ግብሩ 5 ሺ ገደማ ሰዎች የሚሳተፉበት ነው እንደ ፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ናትናኤል ዘለቀ ገለጻ፡፡
ኢዜማ ዛሬ በማካሄድ ላይ ባለው ኮንፈረንስ የእስካሁን እንቅስቃሴዎቹን የሚገመግም ሲሆን ሰፊ ጥናት ሲደረግባቸው ነበር የተባለላቸውን የፖለቲካ ፕሮግራሞቹንና ፖሊሲዎቹን ያስተዋውቃል፡፡
በፓርቲዎች የሚደረገው አጠቃላይ የምረጡኝ ቅስቀሳ ዘመቻ ምርጫው 4 ቀናት ያህል እስከሚቀሩት ድረስ ማለትም እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ይዘልቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዘመቻው ባሳለፍነው ሰኞ የካቲት 8 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ የሚታወስ ነው።
6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም እንደሚካሄድም ይታወቃል፡፡