ምርጫ ቦርድ በፓርላማ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ያገኝ የነበረው የቅስቀሳ የአየር ሰአት ከ60 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን አስታወቋል
በምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰአት ድልድል ላይ ማሻሻያዎች ተደረጉ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰአት ድልድል ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ በፓርላማ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ያገኝ የነበረው የአየር ሰአት ከ60 በመቶ ወደ 5 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉን አስታወቋል፡፡
ለአየር ሰአት ድልድሉ የፓርላማ መቀመጫን መስፈርት ከማድረግ በተጨማሪ 25 በመቶው በእኩል ይደለደላልም ብሏል፡፡
ፓርቲዎች በሚወዳደሩባቸው የፌደራል እና/ወይም የክልል ምክር ቤቶች የሚያቀርቧቸው እጩዎች ብዛት የ40 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
የሴት እና የአካል ጉዳተኛ እጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት በቅደም ተከተል የ20 እና የ10 በመቶ ድርሻ ኖሮት እንደሚደለደልም ነው ካዘጋጃቸው የተለያዩ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጉን ያስታወቀው ቦርዱ የገለጸው፡፡
በምክክሩ ከሴት እጩዎች የድልድል ድርሻ መብዛት እና ስለ ብሮድካስት ባለስልጣን ቀመሩን መሰረት በማድረግ ስለሚኖረው የአሰራር ስነስርአት እና ስለ ግል ሚዲያዎች ሃላፊነት ላይ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ዛሬ በልዩ ሁኔታ ስለሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መመሪያ እና ስለ አርብቶ አደር መራጮች የምዝገባ መመሪያ ከሲቪል ማህበራት ጋር ውይይት መደረጉን ቦርዱ አስታውቋል፡፡