ዘመቻው ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ የሚዘልቅ ነው
6ኛውን ሃገር አቀፍ ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ፓርቲዎች በይፋ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ጀመሩ።
ቅስቀሳው የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሠሌዳ መሠረት ነው።
ቦርዱ ፓርቲዎች ከዛሬ ከየካቲት 8 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ/ም የምረጡኝ የቅስቀሳ ዘመቻ ማድረግ እንደሚችሉ በጊዜ ሠሌዳው አስቀምጧል፡፡
ይህንኑ መሠረት በማድረግም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምርጫ በሚደረግባቸው የወረዳ መዋቅሮቹ የምረጡኝ ቅስቀሳ መጀመሩን አስታውቋል።
በአዲስ አበባ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉበት ዘመቻ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ጭምር ማድረጉንም ነው የገለጸው።
ሆኖም ሽሮሜዳ አካባቢ ለማድረግ አቅዶት የነበረው ዘመቻ «የምርጫ ቅስቃሳ ስለመጀመሩ አናውቅም» ባሉ የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ምክንያት ተስተጓጉሎ ቀርቶብኛል ብሏል።
ዕለቱ ፓርቲዎች ቦርዱ ለይቶ ባወጣቸው አካባቢዎች የሚገኙ እጩዎቻቸውን መመዝገብ የጀመሩበትም ነው፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እጩዎቹን መዝግቦ ማጠናቀቁን በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል፡፡
ገዢው ፓርቲ ብልጽግና የፖለቲካ ፕሮግራሙን (ማኒፌስቶ) እና የምርጫ ምልክቱን ትናንት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሸራተን አዲስ በይፋ ማስተዋወቁም የሚታወስ ነው።