“በኦሮሚያ በተካሄዱ ሰልፎች የተንጸባረቀው መልዕክት የፓርቲዎችን በእኩልነት የመወዳደር መብት ችግር ላይ የሚጥል ነው”-ምርጫ ቦርድ
ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ ተመሳሳይ ድርጊቶችን በመከታተል እጩዎችን እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም ነው ቦርዱ የገለጸው
በገዢው ፓርቲ እና በሌሎች ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈረመውን የቃልኪዳን ሰነድ የሚጥስ እንደሆነም ቦርዱ አስታውቋል
በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለመደገፍ በተካሄዱ ሰልፎች የተንጸባረቀው መልዕክት ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው የፈረሙትን የቃልኪዳን ሰነድ የጣሰ እንደነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
ቦርዱ ሰልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን፤ የመንግስት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በመገናኛ ብዙኃኑ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች መመልከቱንም አስታውቋል፡፡
በሰልፎቹ ላይ የተወሰኑ የመንግስት እና የብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎች ያደረጓቸው ንግግሮች በቦርዱ በህጋዊነት የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎችን በአሉታዊ መልኩ ያነሱ እንደነበሩ ነው ቦርዱ የገለጸው።
በንግግር እና መፈክሮቹ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በአመፃ ተግባር እንደተሳተፉ ተደርጎ ሲገለጽ ነበርም ብሏል፡፡
ፓርቲዎቹን ቦርድ ከሰረዘው እና “ጁንታ” በማለት ከሚጠሩት ህወሃት ጋር አንድ በማድረግ፣ “የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው” ብሎ በመፈረጅ እና “ህገወጥ ናቸው” መባሉ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር ሕግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን የሚጥስ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
በምርጫ አዋጁ አንቀጽ 132 ንኡስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ህግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የስነምግባር ጥሰት መፈጸሙንም ገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሰረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር መሆኑንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡
በመግለጫው አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሰረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነውም ብሏል።
ተግባሩ በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም በጀመረበት ወቅት መፈጸሙ በምርጫው ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡
በመሆኑም በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር እርከኑ ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ቦርዱ አሳስቧል፡፡
ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር ህግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሰረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ፣ የንግግር እና ሌሎች ለህዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከ እጩ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
አብን በሰልፎቹ ከተንጸባረቁት መልዕክቶች ጋር በተያያዘ ቦርዱ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ትናንት በደብዳቤ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡