በረራ ያስተጓጎለው መንገደኛ 15 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተከሰሰ
መንገደኛው 160 ተሳፋሪዎች ባሉበት አውሮፕላን ላይ ረብሻ ፈጥሮ በረራውን አዘግይቷል ተብሏል
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንገደኞች ረብሻ ምክንያት አየር መንገዶች ጉዳት እያስተናገዱ ይገኛሉ
በረራ ያስተጓጎለው መንገደኛ 15 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተከሰሰ።
የአየርላንዱ ሪያን አየር መንገድ በአንድ መንገደኛ ላይ የ15 ሺህ ዶላር ክስ መስርቷል።
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ከሆነ አየር መንገዱ በመንገደኛው ላይ ክስ የመሰረተው ከደብሊን ወደ ስፔኗ ናንዛሮቴ ከተማ እየበረረ የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን በረራ አስተጓጉሏል በሚል ነው።
አውሮፕላኑ 160 መንገደኞችን አሳፍሮ እየተጓዘ እያለ ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ ተሳፋሪ ረብሻ መፍጠሩን ተከትሎ በረራው ተስተጓጉሏል ተብሏል።
ይህ አውሮፕላን በዚህ ሞገደኛ ተሳፋሪ ምክንያት ወደ ናንዛሮቴ ያደርግ የነበረውን በረራ አቋርጦ ወደ ፖርቹጋሏ ፖርቶ ተገዶ አርፏል።
ሁሉም ተሳፋሪዎች እነዚህ ያለ ፕሮግራማቸው በፖርቶ ለረጅም ጊዜ እንዲቆዩ የሆኑ ሲሆን አየር መንገዱ ለተሳፋሪዎች መኝታ እና ሌሎች ወጪዎችን ለማውጣት ተገዷል ተብሏል።
ይህን ተከትሎም መንገደኛው ላደረገው ጉዳት የ15 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፍል ክስ የተመሰረተበት ሲሆን የክሱ ዓላማ ለማስተማር እንደሆነ ተገልጿል።
በረራው በመራዘሙ ምክንያት መንገደኞች በዓልን ከቤተሰቦቻቸው ውጪ እንዲያከብሩ፣ የጊዜ ብክነት እንዲያጋጥማቸው እና አየር መንገዱን ላልተገባ ወጪ መዳረጉ በክሱ ላይ ተጠቅሷል።
በተለይም በበዓል ሰሞን የሚደረጉ በረራዎች ጠጥተው በሚበሩ መንገደኞች ምክንያት መስተጓጎል እያጋጠመ ይገኛል።
የሪያን አየር መንገድ ክስን ተከትሎ በሞገደኛ መንገደኞች ምክንያት በረራቸው የሚስተጓጎልባቸው ሌሎች አየር መንገዶች ተመሳሳይ ክስ ሊመሰርቱ ይችላሉ ተብሏል።