የዩክሬን የድሮን ጥቃት በሩሲያ በረራዎች ከስድስት ስአት በላይ እንዲዘገዩ አደረገ
ኬቭ በ144 ድሮኖች በሩሲያ ላይ ጥቃት አድርሳ ህንጻዎችን ማፈራረሷ ተገልጿል
ፕሬዝዳንት ፑቲን “ሽብርተኝነት” ነው ላሉት የኬቭ የድሮን ጥቃት አጻፋዊ ምላሽ እንደሚወሰድ ዝተዋል
ዩክሬን በሩሲያዋ መዲና ሞስኮ ከፍተኛ የድሮን ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ።
ኬቭ ከትናንት ምሽት ጀምሮ ወደ ሩሲያ 144 ድሮኖችን በመላክ ጥቃት ማድረሷ ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥ 20 የሚደርሱት ከ21 ሚሊየን በላይ ሰዎች በሚኖሩበት በሞስኮ ክልል ተመተው መውደቃቸውን ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ ኬቭ ወደ ሞስኮ በብዛት የላከቻቸው ድሮች በስምንት የሩሲያ አካባቢዎች መውደቃቸው ተዘግቧል።
ራምንስኮይ በተባለች ከተማ የ46 አመት አዛውንትን ህይወት የቀጠፈና ሶስት ሰዎችን ያቆሰለ ጥቃት መፈጸሙን የሞስኮ ክልል አስተዳዳሪ አንድሬይ ቮሮብዮቭ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ከሞስኮ በ50 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው ራምንስኮይ በርካታ የመኖሪያ ህንጻዎች በእሳት መያያዛቸውን የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
70 ድሮኖች በብርያንስክ ክልል መውደቃቸውን የገለጸው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እስካሁን ስላደረሱት ጉዳት ሪፖርት አልተደረገም ብሏል።
የዩክሬን የድሮን ጥቃት ከሞስኮ አራት ዋና ዋና የአውሮፕላን ማረፊያዎች ሶስቱ ለስድስት ስአታት እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል።
ከ50 በላይ በረራዎችም በጥቃቱ ምክንያት የአቅጣጫ ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷል ተብሏል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬን የድሮን ጥቃቶች ንጹሃንን ኢላማ ማድረጋቸውን በመጥቀስ “ሽብርተኝነት” ነው ብለውታል።
ሞስኮ ፈጣን የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድም ዝተዋል።
ሩሲያ በትናንትናው እለት በ46 ድሮኖች በዩክሬን ላይ ጥቃት መፈጸሟ የተገለጸ ሲሆን፥ 38ቱ ተመተው መውደቃቸውን የዩክሬን ጦር አስታውቋል።
ሁለት አመት ያለፈው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የድሮን ውጊያ ከሆነ የሰነባበተ ሲሆን፥ ሁለቱም ሀገራት ርካሽና በፍጥነት ሊሰሩ የሚችሉ ድሮኖችን በማምረት ላይ ተጠምደዋል።