በአሜሪካዋ አላስካ 10 መንገደኞችን የጫነች አውሮፕላን ያለችበት አልታወቀም ተባለ
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አውሮፕላኗን እየፈለጉ ነው ተብሏል
በአሜሪካ ባሁለት ሳምንት ውስጥ ሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ተከስተዋል
በአሜሪካዋ አላስካ 10 መንገደኞችን የጫነች አውሮፕላን ጠፋች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር በሆነችው አሜሪካ የአቪዮሽን አደጋዎች ተደጋግመዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ አንድ የአሜሪካ አየር መንገድ ንብረት የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን ከአነስተኛ ወታደራዊ ሂልኮፕቱር ጋር ግጭት ፈጥረው የ67 መንገደኞች ህይወት አልፏል።
እንዲሁም ባሳለፍነው ሳምንት የአምቡላንስ አገልግሎት የምትሰጥ አነስተኛ አውሮፕላን በመኖሪያ ህንጻ ላይ ተከስክሳ የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል።
አሁን ደግሞ ዘጠኝ መንገደኞችን ጭና ስትጓዝ የነበረች አነስተኛ የመንገደኞች አውሮፕላን ደብዛዋ ጠፍቷል ተብሏል።
ከነ አብራሪው 10 ሰዎች የያዘችው ይህች አውሮፕላን ከአላስካ ኡናላክሊት ተብሎ ከሚጠራው ወደ ኖም በመብረር ላይ ነበረች።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የጠፋችውን አውሮፕላን እየፈለጉ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።
መሰረቱን አላስካ ያደረገው በሪንግ አየር መንገድ 39 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን አንዷ አውሮፕላን ዘጠኝ ተሳፋሪዎችን እና አብራሪውን ይዛ የት እንዳለች እስካሁን አልታወቀም።
ይህ በዚህ እንዳለ በትናንትናው ዕለት የአሜሪካ ወታደራዊ አነስተኛ አውሮፕላን በፊሊፒንስ ተከስክሳ የአራት ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል።