በአሜሪካ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ዙሪያ ምን አዳዲስ መረጃዎች አሉʔ
በአየር ላይ በተከሰተው የአውሮፕላንና ሄሊኮፕተር ግጭት 67 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ “ከአደጋው አንድም ሰው በህይወት አልተረፈም” ብለዋል
ከሄሊኮፕተር ጋር ተጋጭቶ ወንዝ ውስጥ ከገባው የአሜሪካ አውሮፕላን አደጋ የ67 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
60 መንገደኞች እና 4 የበረራ ቡድን አባላትን ያሳፈረው የአሜሪካ ኤርላይንስ አውሮፕላን በዋሽንግተን ዲሲ ሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲቃረብ ከአሜሪካ ጦር ሄሊኮፕተር ጋር መጋጨቱ ይታወቃል።
አደጋውን ተከትሎም በመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት 64 ሰዎች እንዲሁም በሄሊኮፕተሩ ውስጥ የነበሩ 3 ሰዎች በድሩ 67 ሰዎች መሞታቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የመንገደኞች አውሮፕላኑ ከግጭቱ በኋላ በፓቶማክ ባህር ውስጥ መግባቱን ተከትሎ ከ300 በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በምሽትና በአስችጋሪ የአየር ሁኔታ የነፍስ አድን ስራ ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል።
እስካሁን የ27 የአሜሪካ ኤርላይንስ መንገደኞችና በሄሊኮፕተሯ ከተሳፈሩ ሶስት ወታደሮች የአንዱ አስከሬን በድምሮ የ28 ሰዎች አስክሬን ተገኝቶ ከውኃ ውስጥ መውጣቱ ተነግሯል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናድ ትራምፕ ትናንት ምሽት አደጋውን አስመክቶ በዋይት ኃውስ በሰጡት መግለጫ፤ ከአደጋው የተረፈ ሰው የለም ሲሉ ተናግረዋል።
የዋሽንግን የእሳት መከላል ቢሮ ኃላፊ ጆን ዶንሌይ፤ ከአደጋው የተረፈ ሰው አለመኖሩን ተከትሎ ትኩረታችንን ከነበስ አድን ወደ አስክሬን ፍለጋ አድርገናል ብለዋል።
የአሜሪካ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሲን ዱፊ በበኩላቸው አውሮፕላኑ ወደ ባህሩ ውስጥ ዘልቆ ገብቶ በሶስት የተለያየ አቅጣጫ ተቆራርጦ መገኘቱን መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል።
የአሜሪካ ኤርላይንስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮበርት ኢሶም በሮናልድ ሬገን አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን "በትክክለኛው አቅጣጫ" እየተጓዘ እንደነበር በምርመራ መረጋገጡን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በትሩዝ ማህበራዊ ሚዲያቸው ባጋሩት ጽሁፍ "አውሮፕላኑ በትክክለኛ መስመሩ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው እየተቃረበ ነበር፤ ሄሊኮፕተሩ ደግሞ ዘለግ ላለ ጊዜ ወደ አውሮፕላኑ በቀጥታ ሲያመራ ታይቷል" ብለዋል።
"የአውሮፕላኑ መብረት ከርቀት የሚታይ ሆኖ ሳለ ሄሊኮፕተሩ ከፍታውን ወይም አቅጣጫውን ሳይቀይር ከ አውሮፕላኑ ጋር ለምን ተጋጨ የሚለው አጠያያቂ " ነው ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር (ኤፍኤፍኤ) "ሊቀረፍ ይችል ነበር" የተባለውንና ከ60 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የአውሮፕላን ግጭት አደጋ መንስኤ እየመረመረ ነው ተብሏል።
አሁን ላይ የመንገደኞች አውሮፕላን እና የወታደራዊ ሄሊኮፕተሩ የመረጃ መመዝገቢያ ሳጥን (ብላክ ቦክስ) መገኘቱን ተከትሎ የአደጋውን መንስዔ ለማጣርት እየተሰራ መሆኑም ታውቋል።