በሀይቲ በደረሰ የርእደ መሬት አደጋ የ304 ሰዎች ህይወት አለፈ
7 ነጥብ 2 ማጋኒትዩድ ሆኖ የተመዘገበው ርእደ መሬቱ በምእራብ የሀገሪቱ ክፍል ላይ ነው የተከሰተው
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ ለአንድ ወር የሚቆይ የአደጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል
በሀይቲ በደረሰ ከፍተኛ የርእደ መሬት አደጋ ቢያንስ የ304 ሰዎች ሕወት ማለፉ ተገለጸ።
7 ነጥብ 2 ማጋኒትዩድ ሆኖ የተመዘገበው ርእደ መሬቱ በትናትናው እለት ጠዋት በምእራብ የሀገሪቱ ክፍል ላይ መከሰቱም ነው የተገለጸው።
በርእደ መሬት አደጋውም ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው የተነገረ ሲሆን፤ የአምልኮ ስፍራዎች እና ሆቴሎችን ጨምሮ በርካታ ህንጻዎች መፈራረሳቸውም ነው የተገለፀው።
የርእደ መሬቱ ዋንኛ ማእከል በርካታ ሰዎች ከሚኖሩባት ሴንት ሉዊስ ዱ ሱድ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን የአሜሪካ ጆኦሎጂካል ሰርቬይ ማእከል አስታውቋል።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ በርእደ መሬት አደጋው ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ገልጸው፤ ለአንድ ወር የሚቆይ የአደጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ድጋፍ የሚያደርግ ቡድን አዋቅረው ወደ ስፍራው መላካቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በርካታ ሰዎች በህንጻዎች ስብርባሪ ስር ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አሪየል ሄንሪ፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር አንዚህን ሰዎች አፈላለጎ ማግት ነው ሲሉም ተሰምተዋል።
በሌስ ካየስ የሚገኘው ሆስፒታ በተጎጂዎች ስለመሙላታቸውም ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁኔታውን ለመታዘብ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውም ታውቋል።
ሀይቲ ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ በ2010 ላይ በከፍተኛ ርእደ መሬት ተመትታ የነበረ ሲሆን፤ ከ2010 ርድ መሬት ገና በማገገም ላይ እንደነበረች ይታወሳል።