ዓለም በዓመታት ሊቀለበስ ከማይችል የአየር ንብረት አደጋ ውስጥ መውደቋን ቁንጮ የዓለማችን ሳይንቲስቶች አስታወቁ
የዓለም የአየር ንብረት ይዞታ ከመቼውም ጊዜ በላይ መክፋቱን የሚያመለክት ሪፖርት ይፋ ሆኗል
ሳይንቲስቶቹ መሬት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሞቀች ነው ሲሉ አሳስበዋል
የዓለም የአየር ንብረት ይዞታ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ የተባሩት መንግስታት ድርጅት የበይነ መንግስታት የአየር ንብረት ፓናል (IPCC) ተመራማሪዎች አስታወቁ፡፡
ተመራማሪዎቹ የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ እንደሆነ ገልጸው ምናልባትም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ ከሚታሰበው በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
ተመራማሪዎቹ አጥንተውት በ195 ሃገራት የጸደቀ አሳሳቢ የተባለውን የአየር ንብረት ለውጥ የተመለከተ ሪፖርት ይፋ ሆኗል፡፡
ጥንቃቄ በጎደለው የሰው ልጆች ድርጊት የአየር ንብረት ለውጡ ማጋጠሙን የሚያትተው ሪፖርቱ በቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን (pre-industrial levels) የነበረው አማካይ የዓለም የሙቀት መጠን (1.2 ዲግሪ ሴልሺየስ) ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳያልፍ ለመቆጠጠር እ.ኤ.አ በ2015 በፓሪስ የተደረሰው ስምምነት እንደማይሳካ ጠቁሟል፡፡
አማካይ የዓለም የሙቀት መጠኑ በቀጣዮቹ 10 ገደማ ዓመታት ውስጥ ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚያሻቅብም ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
ይህ ለውጡ ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ እየከፋ መምጣቱን ተከትሎ የሚያጋጥም ነው፡፡
ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ እንደ በረሃማነት መስፋፋት፣የበረዶ ግግር መቅለጥ እና ጎርፍ የመሳሰሉትን ተጽዕኖች ለመቆጣጠር ማርፈዷንም ነው ሪፖርቱ የሚያትተው፡፡
ይህም ሳይቀለበስ ምናልባትም ትውልዶች ለሚያልፉባቸው ብዙ ሺ ዓመታት ሊቀጥል እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም አሁንም ፈጥኖ እርምጃዎችን ለመውሰድና የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ከተቻለ የዓለምን የሙቀት ይዞታ ለማረጋጋት የሚቻልበትን መላ ለመዘየድ እንደሚቻል አልሸሸጉም፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ሪፖርቱን ለሰው ልጆች ማንቂያ ደወል ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ሃገራት በተለይ ከፍተኛ የካርቦን ልቀት ያላቸው ያደጉት ሃገራት ጠንካራ እርምጃዎችን እንዲወስዱም ነው ጉቴሬዝ የጠየቁት፡፡
የኮፕ-26 የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ በመጪው ህዳር በስኮትላንድ ግላስጎ እንደሚካሄድ ይታወቃል፡፡