ፖለቲካ
በ2022 የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር በክብረወሰንነት ተመዝግቧል
በዚህ አመት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር 533 መድረሱን የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ገልጿል
የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥርም ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል
በፈረንጆቹ 2022 አመት የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር በክብረወሰንነት መመዝገቡ ተነገረ።
የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (አር ኤስ ኤፍ) ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በዚህ አመት 40 ጋዜጠኞች ታስረው አጠቃላይ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር 533 ደርሷል።
ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል ከግማሽ በላዩ በአምስት ሀገራት ይገኛሉ።
ቻይና 110 ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚዋ ናት፤ በርማ 62፣ ኢራን 47፣ ቬትናም 39፣ ቤላሩስ 31 ጋዜጠኞችን በማሰር ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።
ኢራን ከማሻ አሚኒ ግድያ በኋላ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ጋዜጠኞችን ማሰሯን የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ገልጿል።
መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት ባወጣው አመታዊ ሪፖርት፥ በዚሁ የፈረንጆቹ አመት የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥርም መጨመሩን ያሳያል።
57 ጋዜጠኞች በ2022 ተገድለዋል፤ ይህም በ2021 (48) እና በ2020 (50) ከተመዘገበው ብልጫ ያለው ነው።
ለጋዜጠኞቹ መገደል በዋናነት የዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት መሆኑ ተነስቷል።
የፈረንጆቹ 2022 የጋዜጠኞች እስር እና ግድያ የጨመረበት መሆኑ አሳሳቢ ነው ብሏል አር ኤስ ኤፍ።