በፕሬስ ነፃነት ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት በ101ኛ ደረጃ ያዘች-ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን
ኖርዌይ በፕሬስ ነፃነት 1ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ኤርትራ ከማይመቹ ተብላ የ180ኛ ደረጃ ይዛለች
በአፍሪካ በጋዜጠኝነት ስራዎች እና በመረጃ ነፃነት መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውንም ተገልፀዋል
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከ180 ሀገራት በ101ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው የ101ኛ ደረጃ በፈረንጆቹ 2020 ከነበረችበት በ2 ደረጃዎች ዝቅ ማለትዋንም ነው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን በሪፖርቱ ያመላከተው፡፡
የዓለም ፕሬስ ቀን “መረጃ ለህዝብ ጥቅም” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም እየተከበረ ይገኛል፡፡
bበዩኔስኮ እና በናሚቢያ አዘጋጅነት እየተከበረ በሚገኘው የዓለም ፕሬስ ቀን፤ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሰረት የ180 ሀገራትን የፕሬስ ነጻነት ሁኔታን ዳሰዋል፡፡
ሪፖርቱ በተለይም በኤስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ አውሮፓ ሀገራት የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ የሚጠይቁ ጉዳዮች ለጋዜጠኞች ፈታኝ እንደሆኑ አመላክቷል።
በዘንድሮው ሪፖርት መሰረትም ኖርዌይ ለአምስት ተከታታይ አመታት ጥሩ የፕሬስ ነጻነት አላት ተብላ በአንደኝነት ደረጃ ስትቀመጥ ፊንላንድ እና ስዊድን በተከታታይ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ለፕሬስ ነጻነት ከማይመቹ ሀገራት ውስጥ ደግሞ ቻይና 177ኛ ደረጃ ስትይዝ ቱርክሜንስታን 178ኛ፣ ሰሜን ኮሪያ 179ኛ እና ኤርትራ 180ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ከአፍሪካ ቡሩንዲ 13 ደረጃዎችን አሻሽላ 147ኛ ደረጃ ላይ ስትሆን፣ሴራሊዮን 10 ደረጃዎችን አሻሽላ 75ኛ ደረጃን ይዛለች።
ማሊ ደግሞ 9 ደረጃዎችን አሻሽላ 99ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከ180 አገራት በ101ኛ ደረጃ ላይ በፈረንጆቹ 2020 ከነበረችበት በ2 ደረጃዎች ዝቅ ብላለች።
የሀገራት የፕሬስ ነጻነት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአፍሪካ በጋዜጠኝነት ስራዎች እና በመረጃ ነፃነት መሻሻሎች እየታዩ ነው።