ፖለቲካ
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 32 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ
በጦርነቱ እስካሁን 7 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ሲሰደዱ ከ4 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ተገድለዋል ተብሏል
ዩክሬን የጋዜጠኞች ቀንን በኪቭ አክብራለች
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 32 ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 103 ቀናት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱ ምክንያት ሰባት ሚሊዮን ገደማ ዩክሬናውያን መኖሪያቸውን ለቀው ሲሰደዱ 20 በመቶ የዩክሬን ክፍልም በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ወድቋል።
ዛሬ ይፋ በሆነ መረጃ መሰረት ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ቢያንስ 32 ጋዜጠኞች ተገድለዋል ነው የተባለው፡፡
ይህ የተባለው ዓመታዊውን የጋዜጠኞች ቀን አስመልክቶ በኪቭ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ሲሆን ጋዜጠኞች ብሄራዊ ጀግና ናቸው ሲሉ የዩክሬን የባህል እና መረጃ ሚኒስትር መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ኦሌክሳንድር ትካቼንኮ ጦርነቱን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማድረስ ያለ እረፍት ይሰሩ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡
"ዘላለማዊ ትውስታ ለኢንፎርሜሽን ግንባር ታጋዮቻችን፤ ዛሬ 27/7 የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሁሉ ጀግኖች ናቸው፤ ገለታ ለሁላችሁም ይድረስና የመረጃ ግንባራችን ጠንካራ ነው" የሚል ጽሁፍንም በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል፡፡
በመድረኩ ጋዜጠኞች ስለ ዩክሬን መረጃ ለማድረስ ያለ እረፍት እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን በጦርነቱ ህይወታቸውን ያጡ ጋዜጠኞች ምስል ለህዝብ ይፋ ሆኗል፡፡
የመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት መሰረት 6 ነጥብ 98 ሚሊዮን ዩክሬናውያን መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ 4 ሺህ 183 ሰዎች ሲገደሉ ከ5 ሺህ በላይ ንጹሃን ደግሞ ቆስለዋል፡፡