ታሊባን ካቡልን ከተቆጣጠረ በኋላ 114 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች አፍጋኒስታንን ለቀው ወጥተዋል
በካቡል በሚገኘው የአሜሪካ ወታደሮች ላይ የሮኬት ጥቃት ተሰነዘረባቸው።
አሜሪካ በአፍጋኒስታን የሚገኙ ዜጎቿን እና ለጦሯ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ አፍጋናውያንን የማስወጣቱ ስራ ነገ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካንን ጨምሮ አውሮፓውያን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረው ታሊባን ቡድን ጋር ዜጎቻቸውን እና ረዳቶቻቸውን ከሀገሪቱ እስከ ነገ ነሀሴ 31 ቀን 2021 ድረስ ለማስወጣት በተስማሙት መሰረት በአውሮፕላን በማስወጣት ላይ ናቸው።
እስከ ዛሬ ድረስም ከ114 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች እና በታሊባን ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል የተባሉ አፍጋናውያን ሀገሪቱን ለቀው በአውሮፕላን ወጥተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ዛሬ ሌሊት በካቡል በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ላይ ሮኬቶች መተኮሳቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ወደ ጦሩ የተተኮሱት የሮኬቶች መጠን ያልተገለጸ ሲሆን የአሜሪካ ጦር ግን 5 ሮኬቶች ማክሸፉ ተገልጿል።
በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰው ሽብርተኛው አይኤስአይኤስ ባሳለፍነው ሳምንት በሀሚድ ካርዛይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ ባደረሰው የሽብር ጥቃት 13 የአሜሪካ ወታደሮችን ጨምሮ 130 ዜጎች ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
አሜሪካ የሽብር ቡድኑ ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እያለ በትናንትናው ዕለት በተወሰደ እርምጃ አንድ አጥፍቶ ጠፊ በተሽከርካሪው ውስጥ እያለ መገደሉ ይታወሳል።
ታሊባን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ አዲስ መንግስት እንደሚመሰርት በቃል አቀባዩ ዛብሁላህ ሙጃሂድ በኩል ማሳወቁ አይዘነጋም።