ምእራባውያን ሀገራት ቀነ ገደቡ ሳያልፍ ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት እየተሯሯጡ ነው
ታሊባን የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ለማራዘም ያሳየው ፍላጎት የለም ተብሏል
አሜሪካና አጋሮቿ እስካሁን ትልቅ ነው በተባለው የማስወጣት በረራ የኔቶ ወታደሮችን ጨምሮ 70ሺ ሰዎችን ከአፍጋኒስታን አስወጥተዋል
በአፍጋኒስታን ያሉ የውጭ ወታደሮች የሚወቱቡት ቀነ ገደብ ነሀሴ 25፣2013ዓ.ም እየተቃረበ ባለበት ወቅት፤ ምእራባውያን ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን ሙሉበሙሉ ለማስወጣት በመሯሯጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ ታሊባን የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ለማራዘም ያሳየው ፍላጎት አለመኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እስካሁን ትልቅ ነው በተባለው የማስወጣት በረራ፣ አሜሪካና አጋሮቿ ዜጎቻቸውን፣ የኔቶ(NATO) ወታደሮችንና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አፍጋናውያንን ጨምሮ 70ሺ ሰዎችን ታሊባን ወደ ዋና ከተማ ካቡል ከገባበት ከፈረንጆቹ ነሀሴ 14 ጀምሮ ማስወጣት ችለዋል ተብሏል፡፡
የታሊባን ወደ ዋና ከተማ ካቡል መግባቱ የውጭ ሀገራት ወታደሮችለ20 አመት ያደረጉት ቆይታ እንዲያበቃ አድርጎታል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በአፍጋኒስታን ያሉት የአሜሪካ ወታደሮች ከባድ አደጋ እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል፤የእርዳታ ድርጅቶችም በአፍጋኒስታን ያለው ህዝብ አይቀሬ ለሆነ የሰብአዊ ቀውስ ይዳረጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ባይደን እንዳሉት አሜሪካ ወታደሮቿን እንድታስወጣ ባለፈው አመት የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ተግባራዊ ለማድረግ ጥድፊያ ላይ እንደነበረች ተናግረዋል፡፡ የማስወጣት ሂደቱን ቶሎ መጨረስ እንዲሚገባ የገለጹት ባይደን እያንዳንዷ ተጨማሪ ቀን ተጨማሪ አደጋ ይዛ ትመጣለች ብለዋል፡፡
የአንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራአብ የማስወጣቱ ሂደት እስከ ወሩ የመጨረሻ ደቂቃ ነው ብለዋል፡፡ ታሊባን ያሳድደናል ያሉ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋናውያን የካቡል አየር ማረፊያን ያጨናነቁ ሲሆን ጥቂጥ እድለኞች ብቻ የበረራ ወንበር አግኝተው ወደ ውጭ መውጣት ችለዋል፡፡
አሜሪካ ታሊባን አፍጋኒስታን በመቆጣጠሩ ምክንያት ስጋት ያደረባቸው ዜጎችን ከማስጠጋት ባሻገር ሌሎች ሀገራትም ተጋላጭ ዜጎችን እንዲወስዱ ጠይቃለች፡፡
የአሜሪካ ወታደሮች ከአፍጋኒስታን መውጣታቸውን ተከትሎ ታሊባንን የተቆጣጠሩት ታሊባኖች ከ20 አመታት በኋላ ቤተመንግስት መግባት ችለዋል፤ ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩት ፕሬዘዳንትም ወደ አረብ ኤምሬትስ ተሰድደዋል፡፡