የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚ ቶኒ ብሌር ከአፍጋኒስታን የመውጣት ውሳኔ “አሳዛኝ፣ አደገኛና አላስፈላጊ ነው” ሲሉ ኮነኑ
ብሌር አሜሪካ በ2001 ታሊባንን በማስወገድ በአፍጋኒስታን የከፈተችውን ወረራ በመደገፍ ጦራቸውን ያዘመቱ መሪ ናቸው
ቶኒ ብሌር ውሳኔው ስትራቴጂካዊ ከመሆኑ ይልቅ ፖለቲካዊ ነውም ብለውታል
የአሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣት“አሳዛኝ፣አደገኛና አላስፈላጊ ነው”ሲሉ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ኮነኑ፡፡
ቶኒ ብሌር ውሳኔው ስትራቴጂካዊ ከመሆኑ ይልቅ ፖለቲካዊ ነው ሲሉም ነው “Tony Blair Institute for Global Change” በተሰኘው የተቋማቸው ድህረ-ገጽ ያሰፈሩት፡፡
ቶኒ ብሌር " የአፍጋኒስታንና ህዝቦቿ መገለል አሳዛኝ፣አደገኛ እና አላስፈላጊ ነው"ም ብለዋል፡፡
ከአፍጋኒስታን የመውጣቱ ውሳኔ የምእራቡ ዓለም ቁርጠኛ አለመሆኑ የሚያመላክት ነው ያሉት ብሌር ሁኔታው አሳሳቢ በመሆኑ ጣልቃ ገብነት እንዲኖርም አሳስበዋል፡፡
"አሁን ላይ የምእራቡ ዓለም ቦታ የት እንደሆነ ዓለም እርግጠኛ መሆን አይችልም፤ ምክንያቱም በአፍጋኒስታን የተላለፈው ውሳኔ ከስትራቴጂካዊነቱ ይልቅ ፖለቲካዊነቱ ያመዝናልና"ም ነው ብሌር ያሉት፡፡
እ.ኤአ. ከ1997 እስከ 2007 እንግሊዝን የመሩት ቶኒ ብሌር የመስከረም (ሴፕቴምበር 11) ጥቃቶች ምክንያት አሜሪካ በ2001 ታሊባንን በማስወገድ በአፍጋኒስታን የከፈተችውን ወረራ በመደገፍ ጦራቸውን ወደ አፍጋኒስታን የላኩ መሪ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣቱን ተከትሎ የታሊባን ታጣቂዎች ሀገሪቱን በፍጥነት መቆጣጠራቸው በርካቶችን ያስገረመ ክስተት ነው፡፡
ላለፉት በርካታ አመታት የአሜሪካ መሪዎች በተለያዩ ተልእኮዎች ተሰማርተው የሚገኙ ወታደሮቻቸውን ቁጥር እንደሚቀንሱ በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡