የቀድሞው ሚኒስትር የአሁኑን ስራ የመረጡት በተማረበት ሙያ ስራ ስላጣሁ ነው ብሏል
የቀድሞው የአፍጋኒስታን የኮሙንኬሽን ሚኒስትር የነበሩት ሳይድ ሳዳት ወደ ጀርመን ተሰደው በእቃ አመላላሽነት ተቀጥረው ስራ ጀምረዋል።
የቀድሞው ሚኒስትር ካቡልን ለቀው ወደ ጀርመን ከተሰደዱ በኋላ በላይፕዝሽ ከተማ በሳይክል እቃ አመላላሽነት ተቀጥረው በስራ ላይ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሳዳት እንዳሉት “ሰዎች ይሄንን በመስራቴ ሊተቹኝ ይሞክራሉ ነግር ግን ስራዬን በመስራቴ ምንም ጥፋተኝነት አይሰማኝም፤ ሌሎች ፖለቲከኞችም ራሳቸውን ከመደበቅ ይልቅ የእኔን ፈለግ ቢከተሉ የተሻለ ነው” ብለዋል።
የሚኒስትሩ ቤተሰቦች አሁንም በአፍጋኒስታን የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ከካቡል አንደሚወጡ ተስፋ እንዳላቸው ለሮይተርስ ተናግሯል።በጀርመን ሀገር ስራ ለማግኘት የሀገሪቱን ቋንቋ መቻል የግድ መሆኑ በተማረበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ቴሌኮም ሙያ ስር ማግኘት እንዳልቻለም የቀድሞው ሚኒስትር ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ታህሳስ ወደ ጀርመን የተሰደደው የቀድሞው የአፍጋን የኮሙንኬሽን ሚኒስትር ህይወቱን ለማርዘም እና የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሲል በሳይክል እቃ የማመላለስ ስራን ለመጀመር መገደዱንም ተናግሯል።
በአሽራፍ ጋኒ የሚመራው የአፍጋኒስታን መንግስት ታሊባን አገሪቱን በሀይል መቆጣጠሩን ተከትሎ ነበር የአገሪቱ ህጋዊ መንግስት የፈረሰው።
በዚህም ምክንያት አሽራፍ ጋኒ ወደ ጎረቤት አገር ኡዝቤኪስታን የተሰደዱ ሲሆን የቀድሞው ፕሬዘዳነት በካቡል የባሰ ጦርነት ተከስቶ ጉዳት ለመቀነስ ሲባል እንደተሰደዱ መናገራቸው ይታወሳል።
በአፍጋኒስታን የትጥቅ ትግል ሲያካሄድ የነበረው ታሊባን የአሜሪካ መንግስት ወታደሮቹን ካስወጣ በኋላ የአፋጋኒስታንን ዋና ከተማ ካቡል መቆጣጠር ችሏል፡፡ ምእራባውያን ሀገራት ታሊባን የሀገሪቱን መንግስት መቆጣጠሩን ተከትሎ ወታደሮቻቸውን ለማስወጣት በመሯሯጥ ላይ ናቸው፡፡